ኢንቨርቲንግ ዘ ፒራሚድ| ምዕራፍ ስምንት – ክፍል ሦስት

የጆናታን ዊልሰን Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics የአማርኛ ትርጉም የዛሬው መሠናዶ የስምንተኛው ምዕራፍ ሦስተኛ ክፍልን ይዞላችሁ ቀርቧል።


 ከ1950ዎቹ በፊት በነበሩት ዓመታት በእንግሊዝ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ላይ ባመዘነ የቅብብል ሒደት የሚካሄድ ጨዋታን (Possession-Based Passing Game) የሚተካከል የእግርኳስ ታክቲካዊ እድገት እምብዛም አልተለመደም ነበር፡፡ ከ1940ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ ቶተንሃሞች በ<Push-And-Run> የአጨዋወት ሥልት ስኬታማ ቢሆኑም በጥርጣሬ ዓይን ከመታየት ግን አላመለጡም፡፡ የተቀረው ዓለም በጨዋታው ቴክኒካዊ ጉዳዮች ከፍተኛ እመርታ ሲያስመዘግብ፣ የመከላከል አደረጃጀትን በሰለጠነ መንገድ ሲያዋቅር እና ፍሰቱን ጠብቆ የሚዋልል እንቅስቃሴ ሲያደርግ የብሪታንያ እግርኳስ ግን በነበረበት መርገጡን ቀጠለበት፡፡ በጣልያን ሄሌኒዮ ሄሬራ የሲውዘርላንዳዊውን አሰልጣኝ ካርል ራፕን የጥንቱን ጥብቅ የመከላከል ሥርዓት <ካቴናቺዮ>ን ተቀብሎ እያሻሻለው እንደተጠቀመበት ሁሉ በእንግሊዝም ነባሩ የአጨዋወት ዘዴ ተመራጭ ሆነ፡፡ ለዚህኛው የጨዋታ ዘይቤ የድጋፍ ሙግት የሚያቀርቡት  ወገኖች ሥልቱ ተጨባጭ፣ ነባራዊና ተግባራዊ እውነታን (Pragmatism) የመከተል ውጤት ስለመሆኑ ቢከራከሩም መሰረታዊ ምክንያቱ ብሪታኒያውያኑ ዘንድ ካለው ሥር የሰደደ ስጋት ጋር መገናኘቱ ነው፡፡ የሃገሪቱ ቡድኖች ረዘም ላሉ ጊዜያት ቀደምት የእግርኳስ ባህላቸው ላይ ሙጥኝ ማለታቸው ራሳቸውን ለተጋጣሚ በቀላሉ ተጋላጭ ከማድረግ ለመታደግ እንደሆነ ይነገርባቸዋል፡፡ ከድሮም ክህሎት አልያም በጥልቀት ማሰብ የሚያሻው ማንኛውም የጨዋታው እንቅስቃሴ እምብዛም እምነት አልተጣለበትም፤ ይልቁኑ በሃገሪቱ እግርኳስ አካላዊ ጥንካሬ ከፍተኛ ትኩረት ሲቸረው ከርሟል፡፡ ጭንቅላቱ ላይ በደረሰበት ግጭት ሙሉ መለያው በደም ተጨማልቆም ቡድኑን ከማበረታታት ወደኋላ ያላለውን ቴሪ ቡቸር የሚያሳየው አስገራሚ ምስል ከ1966ቱ የዓለም ዋንጫ ድል እኩል የእንግሊዝ እግርኳስ መገለጫ ሆኖ የመቅረቱ ጉዳይ የአጋጣሚ ሊባል አይችልም፡፡ ተጫዋቹ ግንባሩ ዙሪያ በፋሻ ተጠቅልሎ ሃገሩ ለ1990ው የዓለም ዋንጫ የመጨረሻ ማጣሪያ ከሲውዲን ጋር ያለ ጎል አቻ ተለያይታ በውድድሩ ተካፋይነቷን እስክታረጋግጥ ድረስ በከፍተኛ ወኔ የቡድን አጋሮቹን ሲያነቃቃ የዋለው የያኔው የሬንጀርስ መሃል ተከላካይ የአካል ብቃት፣ ጥሩ ተክለ ሰውነትና ጠንካራ የስነ ልቦና ዝግጅት የሚፈልገው የብሪታኒያ እግርኳስ ማሳያ ሆኗል፡፡ በሃገሪቱ የተለመደውን አጨዋወት ይዞ መቀጠልም ዓይነተኛ ባህርይ ሆኖ ዘልቋል፡፡ በ1997 በሮም ጣልያንና እንግሊዝ ለፈረንሳዩ የዓለም ዋንጫ ውድድር ለማለፍ ወሳኝ የማጣሪያ ፍልሚያቸውን ሲያደርጉ ባለሜዳዋ ሃገር ግጥሚያውን የማሸነፍ ቅድመ ግምት አግኝታ ነበር፡፡ በወቅቱ እንግሊዝ የማያስተማምን ብቃት ላይ ብትገኝም ከጣልያኖቹ አንጻር ተቃራኒውን የአጨዋወት መንገድ መረጠች፡፡ ይሁን እንጂ ጣልያን ጨዋታውን በበላይነት ለማጠናቀቅ ከመጣር ይልቅ አጠቃላይ የፍልሚያውን መልክ አሉታዊ ገጽታ አላበሰችው፡፡ ተጫዋቾቿ በመሃለኛው የሜዳ ክፍል ላይ ብቻ የተገደበና እጅጉን ዝግ ባለ ፍጥነት የሚካሄድን ቅብብል መደበኛ ተግባራቸው አድርገው አመሹ፤ ያለ አግባብ ሰዓት ማባከኑ ደግሞ ከፍልሚያው የተጠበቀውን ሞቃት ድባብ አብርዶ የማራኪነቱን ለዛ አሳጣው፡፡ ከዚያ ቀደም በ1989 በስቶክሆልም እንግሊዞች ከሲውዲን ጋር ሲጫወቱ በጥልቀት ወደኋላ አፈገፈጉ፤ በራሳቸው የሜዳ ክልልም በመሆን ጠንክረው ተከላከሉ፤ 0-0 አቻ ተለያዩ ፤ ፈታኙን ጨዋታም በብቃት ተወጡት፡፡ ሳይመን ኩፐር ይህኛው መንገድ በእያንዳንዱ አጋጣሚ ከፍተኛ ሽንፈትን ለማስወገድ ሲባል መሸሽንና ማድፈጥን እንደ መጨረሻ አማራጭ የማድረግ ልማድ እንደሆነ ይናገራል፡፡ እንዲያውም ጸሃፊው ይህን የማፈግፈግ ባህል በ1940 የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ፈረንሳዮችና እንግሊዞች በሰሜናዊ ፈረንሳይ የባህር ደርቻ የከተመው ሰራዊታቸው በጀርመን ድባቅ እንዳይመታ ሲሉ ወደ ሶስት መቶ ሰላሳ ሺህ የሚደርስ ወታደር እንዲሸሽና ወደ ሃገሩ እንዲገባ ከወሰኑበት የ<Dunkirk> ውሳኔ ጋር ያመሳስለዋል፡፡

በእንግሊዝ እግርኳስ ከጥንት ጀምሮ ሲተገበር ለነበረው የአጨዋወት ሥርዓት ስታን ኩሊስን ተወቃሽ ማድረግ እርባና ቢስ ተግባር ነው፡፡ በ1950ዎቹ የሃገሪቱ እግርኳስ ጸሃፊዎች በውጤታማነቱ ሰበብ በመላው እንግሊዝ ሥር ለሰደደውና ወጥ የጨዋታ ሥልት ተደርጎ ለተለመደው የእግርኳስ አቀራረብ ኸርበርት ቻፕማንን በተጠያቂነት እንደሚያነሱ ሁሉ ስታን ኩሊስም የዚሁ ወቀሳ ተቋዳሽ ሆኗል፡፡ ጥንት ዊሊ ሜይዝል ከወንድሙ ሑጎ ሜይዝል ጋር ስለ እግርኳስ ሲወያይ በቀሰመው እውቀት ላይ ተመስርቶ ያመነባቸው የእነዚያ ምናባዊ እሳቤዎች ተግባራዊነት አጓግቶት በአቋሙ ቢጸና ኖሮ ፊቱን ወደ ቀደመው ባህላዊ የአጨዋወት ሥርዓት  ይመልስ ነበር፡፡ ቻፕማን ከመሞቱ በፊት ቢሆን ግን ሜይዝል ከቶውኑም ወደኋላ መመለስን አያስበውም፡፡ በተጨማሪ ውጤታማነት ከማራኪ አቀራረብ በላይ ዋጋ ተችሮት ዋነኛ የጨዋታው ግብ ከሆነም የተጫዋቾች ተክለ ሰውነት፣ አካል ብቃትና ወኔ ላይ ማተኮር ስህተት ሊሆን አይችልም፡፡ ከሃንጋሪው ድንገተኛና አስደንጋጭ ሽንፈት አስራ ሶስት ዓመታት በኋላ እንግሊዝ የዓለም ዋንጫን አሸንፋለችና፡፡ ወሳኙና ጠቃሚው መነሻ የአጨዋወት ሥርዓት (Method) መዘርጋት  ሲሆን ንድፈ-ሐሳብ ተከትሎ የሚመጣ ጉዳይ ነው፡፡

በ1960ው የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የኩሊሱ ዎልቭስ በሄሬራው ባርሴሎና ከፍተኛ ብልጫ ተወስዶበት ሊሆን ይችላል፡፡ ጥቂት ዓመታት ወደኋላ ተጉዘን ሰናይ ግን የእንግሊዙ ክለብ ወሳኝ ድሎችን በትልልቅ ቡድኖች ላይ መገናጸፍ ችሎ እንደነበር እንረዳለን፡፡ በ1953 የክረምት ወቅት በሞሊነክስ የስታዲየም መብራት ምሰሶዎች ተተከሉ፤ በመስከረም ወር ዎልቭስ ከደቡብ አፍሪካ ብሄራዊ ቡድን ጋር ባከናወነው ጨዋታ መብራቶቹ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ ዋሉ፡፡ ከብዌኖስ አይረስ የተጋበዘው ሬሲንግ ክለብ በዎልቭስ 3-1 ተረታ፡፡ <ኤክስፕሬስ> የተሰኘ ጋዜጣ ላይ ሐሳበ-ግትሩ ጋዜጠኛ ዴዝሞንድ ሃኬት “በፍጥነትና ከፍተኛ ወኔ የሚካሄደው የእንግሊዝ እግርኳስ አጨዋወት የዓለም ምርጡ የጨዋታ ዘይቤ ነው፡፡ ዎልቨርሃምፕተን ዎንደረርሶች ደግሞ ይህን ዘዴ በስኬትማነት ይተገብሩታል፡፡” ብሎ ጻፈላቸው፡፡ በእርግጥ ያኔ ዎልቭሶች ትልልቆቹን የአውሮፓ ክለቦችም ድል ይነሱ ነበር፡፡ ዳይናሞ ሞስኮን 2-1፣ ስፓርታክን ደግሞ 4-0 ማሸነፍ ችለዋል፡፡ ያለምንም ማንገራገር ከሁሉም በላይ በክለቡም ሆነ በሃገሪቱ ታሪክ ሁሌም እጅጉን የሚታወሰው ግጥሚያ ግን በታህሳስ ወር-1954 የእንግሊዙ ዎልቭስ፥ ፑሽካሽ፣ ዚቦር፣ ቦዚክ፣ ኮዚክ እና የመሳሰሉትን ታላላቅ ተጫዋቾች ከያዘው ኻኖቭድ ጋር ያደረገው ጨዋታ ነው፡፡ ሃንጋሪ እንግሊዝን ሁለት ተከታታይና አሸማቃቂ ሽንፈቶችን ካከናነበቻት በኋላ የእግርኳስ ፈጣሪዋ ሃገር የበቀል በትሯን የምታሳርፍበትን እድል አገኘች፡፡

በ1954ቱ የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ከጀርመን ጋር ባደረገችው ጨዋታ በክረምቱ ሳቢያ የጨቀየው ሜዳ ሃንጋሪን ምን ያህል እንዳስቸገራት ያስታወሰው ስታን ኩሊስ እግርኳሳዊ ፍልሚያው በሚከናወንበት ማለዳ ልምድ እንዲቀስሙ ተብሎ ከክለቡ ተጠባባቂ ቡድን ዋናውን ቡድን የተቀላቀሉትን ሶስት ወጣቶች ሜዳውን በውሃ እንዲያርሱት አዘዛቸው፡፡ አንደኛው በወቅቱ አስራ ስድስት ዓመቱ ላይ ይገኝ የነበረው ሮን አትኪንሰን ነው፡፡ አትኪንሰን ” ‘ይሄ ሰውዬ ከአዕምሮው  አይደለም ማለት ነው፡፡’ ብለን አሰብን፤ ‘ታህሳስ እኮ ነው፥ ለአራት ቀናት ያለማቋረጥ ይዘንብ የለ እንዴ!’ አልን፡፡” ይላል የኩሊስን የህይወት ታሪክ ላዘጋጀው ጂም ሆልደን በሰጠው ቃለ-ምልልስ ላይ፡፡

ጨዋታው በተጀመረ በመጀመሪያዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች ኻኖቭዶች ሁለቴ ዎልቭሶች ላይ ጥቃት አደረሱ፡፡ አከታትለውም ሁለት ግብ አስቆጠሩ፡፡ ነገርግን ደቂቃዎች እየገፉ ሲሄዱ ኻኖቭዶች ሁኔታዎች እየከበዷቸው መጡ፡፡ አትኪንሰን ትርክቱን ይቀጥላል- ” ኻኖቭዶች ቀስ በቀስ መጓተት ጀመሩ፤ የተጫዋቾቻቸውን ተዓምራዊ አብዶዎች ጭቃው ዋጠው፡፡” ቀድሞ ሜዳው ይህን ያህል እንዲጨቀይ የወሰነው ኩሊስ በዕረፍት ሰዓት ተጫዋቾቹን ረዣዥም ቅብብሎች እንዲከውኑ፣ ኳስን ለፊት መስመር ተሰላፊዎች በፍጥነት እንዲያደርሱ እና እጅጉን ተጠጋግተው የተሰለፉትን የኻኖቭድ መስመር ተከላካዮች እንዲያስጨንቁ መከራቸው፡፡ ሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ አራተኛው ደቂቃ ላይ ዎልቭሶች የሚፈልጉትን ማነሳሻ ግብ በጆኒ ሃኖክስ አማካኝነት በፍጹም ቅጣት ምት አስቆጠሩ፡፡ 

” ዎልቭሶች በሒደት ወገባቸውን አጠበቁ፤ ቁጥራቸው  እጥፍ የሆነ ያህል በሙሉ ኃይላቸው ሜዳውን ሞሉት፤ እያንዳንዱ የሜዳ ክፍል ላይ እንደፈለጉ ይቦርቁ ጀመር፡፡ ይሄኔ መጫወቻ ሜዳው በጭቃ እጅጉን ተናጠ፤ እንደ ወፍራም ማጣበቂያም ይለነቁጥ ያዘ፡፡ የሞሊነክስ ታዳሚ ስታዲየሙን አናጋው፤ በባህር ዳርቻ እንዳለ ማዕበልም የደጋፊው ጩኸት በረታ፤ ‘አለቀላችሁ!’ እያለም ተጋጣሚውን ማራዱን ቀጠለ፡፡” ብሏል ጂኦፍሪ ግሪን በጽሁፉ፡፡ ወደ ስታዲየሙ የመጣባት ብስክሌት ተገጭታ መጠነኛ ጉዳት ደርሶበት የተሰለፈው ዴኒስ ዊልሾው እንዲህ የተጋጋለው ፍልሚያ ሊያበቃ አስራ አራት ደቂቃዎች ሲቀሩ ለመሃል አጥቂው ሮይ ስዊንቦርን ኢላማውን የጠበቀ ተሻጋሪ ኳስ ላከለት፤ የመሃል አጥቂው በግንባሩ የአቻነቷን ጎል አስቆጠረ፡፡ በዘጠና ሰከንድ ልዩነት ውስጥ የእነዚሁ ጥምር ተጫዋቾች ቅብብል በድጋሚ የማሸነፊያ ግብ አስገኘ፡፡

እንግሊዝ በሃንጋሪ በደረሰባት አስከፊ ሽንፈት ለአንድ ዓመት ያህል በቁጭት ስትማቅቅ ኖራ ዎልቭስ ኻኖቭድ ላይ ባሳካው ድል ምክንያት ተካሰች፡፡በሃገሪቱ ደስታና ፈንጠዝያ ሰፈነ፡፡ ” ከዚህ በኋላ በህይወቴ ከዚህ የላቀ ልብ ሰቃይ ታሪክ የምጽፍበት ጊዜ ይኖረኛል ብዬ ፈጽሞ አላስብም፡፡” ሲል ጋዜጠኛ ፒተር ዊልሰን በ<ዴይሊ ሚረር> ላይ ጻፈ፡፡ ቻርሊ ቡቻንም በ<ኒውስ ክሮኒክል> አምዱ ” በቀጣይ  እንደ እነዚህ ያሉ በርካታ አጓጊ ድሎችን ለማየት ቀሪ እድሜዬ የሚፈቅድልኝ አይመስለኝም፡፡” ሲል ጽፏል፡፡ አክሎም የእንግሊዛውያኑ የአጨዋወት ሲስተም የውጤታማነት ማረጋገጫ መሆኑንም ገለጸ፡፡ <ዴይሊ ሜይል> ጋዜጣ በበኩሉ በድሉ ሰበብ የታየውን የቡረቃ ስሜት አርዕሰተ ዜና አደረገው፤ 

” የዓለም ሻምፒዮኑ ዎልቭስ ይክበር!” የሚል መወድስም ይዞ ወጣ፡፡ ይህም አዋጅ ጋብሬል ሃኖትን እጅግ አስቆጣው፤ በእንግሊዞቹ ዘንድ የሰረጸውን የእግርኳስ ልዕለ ኃያልነት አመለካከት ከሥሩ ለመመንገልነና ተዓብዮው ሐሰት መሆኑን ለማሳየት ቆርጦ ተነሳ፤ የአውሮፓ ክለቦች ዋንጫ ውድድር እንዲጀመርም ገፋፋ፤ ጣረና ተሳካለት፡፡ 

ዊሊ ሜይዝል የፈንጠዝያው ገለልተኛ ታዛቢ ሆኖ ቆየ፤ እንዲያውም ኻኖቭድ በዎልቭስ ከመሸነፉ ቀደም ብሎ በዩጎስላቭ ሊግ ከመሪው ፓርቲዛን ርቀው ሰባተኛ ደረጃ ላይ ይገኙ በነበሩትና የሚዋልል አቋም በሚያሳዩት ሬድ ስታር ቤልግሬዶች መረታቱንም ጠቆመ፡፡ ” በወቅቱ እጅግ ጠንካራ ብቃት የሚያሳዩትን ፓርቲዛኖች እንኳ ማንም ‘የዓለም ሻምፒዮኖች!’ ብሎ አልሰየማቸውም፡፡ ተፈጥሯዊ ቢሆኑ እንኳ በመሥፈርት ደረጃ ረግረጋማ ሜዳዎች ብቻ የዓለም ሻምፒዮኖች የሚመዘኑባቸው ምርጥ የመጫወቻ ሥፍራዎች ተደርገው ሊወሰዱ እንደማይገባ አስተያየት መስጠት ነበረብኝ፡፡” ይላል ሜይዝል፡፡ በእርግጥ ያኔ ተክለ-ሰውነትና ቴክኒክ ለንጽጽር ቢቀርቡ እንግሊዝ ከሁለቱም ቀላቅላ የተሻለ አቅም መፍጠር የሚያስችል መሰረት ነበራት፡፡ ይሁን እንጂ ቀጥለው በመጡት ዓመታት የታየውም 

በ”… ይሆን ነበር፡፡” ብቻ የቀረው አስተያየት ከባዶ ማጽናኛነት የዘለለ ፋይዳ እንዳልነበረው ነው፡፡ የሙኒኩ የአውሮፕላን አደጋ በፈጠረው ቀውስ ሳቢያ ማንችስተር ዩናይትድ እጅጉን ተዳክሞ ዎልቭሶች በ1958 እና 1959 በተከታታይ የሊጉን ዋንጫ አነሱ፤ በ1960 ደግሞ የእግርኳስ ማህበሩን ድል ተቀዳጁ፡፡ ነገርግን ይህን ስኬት ከሃገር ውጪ ሊያሳኩ አልቻሉም፡፡ በ1955 በተጀመረው የአውሮፓ ክለቦች ዋንጫ ላይ የነበረውን የፉክክር ሚዛን በማስጠበቅ ረገድ ያሳደሩት ተጽዕኖ እዚህ ግባ የሚባልም አልነበረም፡፡ በውድድሩ የሚታወስ አሻራ ማሳረፍ እንኳ ተስኗቸው ታዩ፡፡ እናም በበርሚንግሃም አየር ማረፊያ ሄሌኒዮ ሄሬራ ስለ እግርኳሳቸው የሰነዘረው የሰላ ትችት እንግሊዞች ሊጎነጩት የከበዳቸው መራራ እውነት ሆነባቸው፡፡

ይቀጥላል...


ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡ ባለፉት አስራ ሦስት ዓመታትም አስር መፅሐፍትን ለህትመት አብቅቷል፡፡