ዋሊያዎቹ በባህር ዳር ልምምዳቸውን እያከናወኑ ይገኛሉ

ከትላንት በስትያ ባህር ዳር የደረሰው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን መቀመጫውን በዩኒሰን ሆቴል በማድረግ ልምምድ እያከናወነ ይገኛል።

ካሜሩን ላይ በ2020 ለሚደረገው የቻን ውድድር ለማለፍ የማጣሪያ ጨዋታዎችን እያደረጉ የሚገኙት ዋሊያዎቹ ማክሰኞ አመሻሽ ባረፉበት ሆቴል ከሰሩት የ45 ደቂቃ የጂምናዚየም ልምምድ በኋላ ትላንት ሁለት ጊዜ (ጠዋት እና አመሻሽ) የሜዳ ላይ ተግባራት አከናውነዋል።

ዛሬም ልምምዳቸውን የቀጠሉት ዋሊያዎቹ ለሶስት ሰዓታት ያኽል በባህር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም የተግባር ስራ አከናውነዋል። ረፋድ 4 ሰዓት የጀመረው የልምምድ መርሃ ግብር ከኳስ ጋር ያሉ ስራዎች ሙሉ ለሙሉ የተካተቱበት ነበር። ተጨዋቾቹ ካሟሟቁ በኋላ የአሰልጣኝ ቡድን አባላቶቹ ቡድኑን ለአራት ከፍለው በሩብ ሜዳ ለየት ያለ ልምምምድ ሲያሰሩ ተስተውሏል። ከዚህ ልምምድ በመቀጠል ቡድኑ ለሁለት ተከፍሎ የሙሉ ሜዳ ጨዋታ ተከናውኗል። በዚህ የልምምድ መርሃ ግብርም የቡድኑ አምበል አስቻለው ታመነ መጠነኛ ጉዳት አስተናግዶ ልምምዱን አቋርጦ ወጥቷል።

ከዛሬ ጀምሮ እስከ ቅዳሜ በቀን አንድ ጊዜ በባህር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም ልምምዳቸውን የሚያከናውኑት ዋሊያዎቹ እንዳስፈላጊነቱ የጂምናዚየም ልምምድ ለሚያስፈልጋቸው ተጨዋቾች ዛሬን ጨምሮ የተለየ ልምምድ ባረፉበት ዩኒሰን ሆቴል እንደሚሰጥ አሰልጣኙ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል።

በዛሬው የልምምድ መርሃ ግብር መለስተኛ ጉዳት ካስተናገደው አስቻለው ታመነ ውጪ የፋሲል ከነማው ያሬድ ባዬ በልምምዱ ሙሉ ለሙሉ አልተሳተፈም። ቡድኑ ለሶስት ሰዓታት ልምምድ ሲሰራ በቦታው የነበረው ያሬድ ከክለቡ (ፋሲል ከነማ) ጋር የቅድመ ውድድር ዝግጅት ሲያደርግ ባጋጠመው የጉልበት ጉዳት ከልምምዱ ውጪ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

የፊታችን እሁድ ከዩጋንዳ ብሄራዊ ቡድን ጋር በባህር ዳር የወዳጅነት ጨዋታ የሚያደርጉት ዋሊያዎቹ ከፋሲል ከነማ ጋር ሊያደርጉት የነበረው የወዳጅነት ጨዋታ መሰረዙ ታውቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ