የኢትዮጵያ ቡናው ተከላካይ ለጋዜጠኛ ምስጋናው ታደሰ የገንዘብ ድጋፍ አደረገ

የኢትዮጵያ ቡናው የተከላካይ መስመር ተጫዋች ተመስገን ካስትሮ በህመም ላይ ለሚገኘው ጋዜጠኛ ምስጋናው ታደሰ የገንዘብ ድጋፍ አደረገ።

ጋዜጠኛ ምስጋናው እግሩ ላይ በገጠመው ጉዳት ህክምናውን እየተከታተለ እንደሚገኝ እና ለተሻለ ህክምና ከሀገር ውጭ ታክሞ ሙሉ ጤንነቱ ተመልሶ ወደሚወደው ሙያ እንዲመለስ ስፖርት ወዳዱ ህብረተሰብ አቅሙ በፈቀደ መጠን ድጋፍ እንዲያደርግለት መጠየቁ ይታወሳል።

ይህን ተከትሎ በተወሰነ መልኩ የሚደረገው ድጋፍ የቀጠለ ሲሆን የኢትዮጵያ ቡና ተከላካይ ተመስገን ካስትሮ ጋዜጠኛ ምስጋናው ከደረሰበት ህመም እንዲያገግም በማሰብ በግሉ 20 ሺህ ብር የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል። ተመግገን ካስትሮ ያደረገው በጎ ተግባር ሌሎችም አካላት መሰል ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ በር የሚከፍት ነው።

በዚህ ጉዳይ ላይ የሚናገረው ጋዜጠኛ ምስጋናው የኢትዮጵያ ተጫዋቾች ማኅበር የ10 ሺህ ብር እና ተጫዋች ኤፍሬም ወንደሰን በግሉ የሚያደርገው ድጋፍ እንዲሁም የሙያ ባልደረቦቹ አጠቃላይ የስፖርት ቤተሰቡ እያደረጉለት ባለው ነገር ምስጋናውን አቅርቦ በአሁኑ ሰዓት ለቀናት ይከታተል የቆየውን በመርፌ ይሰጥ የነበረውን ህክምና አጠናቆ የመድኃኒት ህክምና የጀመረ በመሆኑ ከቤተሰቦቹ ጋር ለተወሰ ቀናት ቆይታ ለማድረግ ወደ ትውልድ ከተማው መሄዱን ገልፆልናል።

ምስጋናውን መደገፍ የሚፈልግ አካል በነዚህ የባንክ አካውንቶች መጠቀም ይቻላል…

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ – 1000268456639

አዋሽ ባንክ – 01320148371700


© ሶከር ኢትዮጵያ