የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ሊያገኝ ነው

የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ጨዋታዎች በአዲስ ቲቪ (አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ) የቀጥታ ስርጭት እንደሚያገኝ ታውቋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የዘንድሮ ውድድር ከጥቅምት 22 እስከ ኀዳር 7 በአዲስ አበባ ስታዲየም በስምንት ክለቦች መካከል እንደሚደረግ የተገለፀ ሲሆን ውድድሩም በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ሊተላለፍ እንደሆነ ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ተቋም የሆነው አዲስ ቲቪ (አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ) ይህን ውድድር በቀጥታ ስርጭት የሚያስተላልፍ ሲሆን ከዕጣ ማውጣት ሥነ-ስርአት ጀምሮ የተመረጡ ጨዋታዎችም ሽፋን ያገኛሉ፡፡ በመጪው ሐሙስ በሚሰጥ መግለጫም ይፋ እንደሚደረግም ይጠበቃል፡፡

ስፖንሰር አድራጊ ድርጅቶችን እያፈላለገ የሚገኘው የአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ፌድሬሽን የዚህ ዋንጫ አሸናፊን ጨምሮ እስከ ሦስተኛ ለሚወጡት ከፍተኛ የገንዘብ ሽልማት እና ተሳትፎ ለነበራቸው ክለቦች ደግሞ በተሳታፊነታቸው ብቻ በስጦታ መልክ ገንዘብ ለማበርከት እንደታሰበ የተነገረ ሲሆን የስታዲየም መግቢያ ትኬቶች እና ሌሎች ስራዎችን በዘመናዊ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግም በዝግጅት ላይ መሆኑንም ሰምተናል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ