የአዲስ አበባ ከተማ እግርኳስ ክለብ እጣ ፈንታ ምን ይሆን?

በርካታ ውስብስብ ጉዳዮች እየታዩበት ያለው የአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ክለብ የመቀጠሉ ነገር አጠራጣሪ ሆኗል።

በ2004 የተመሠረተው እና በ2008 ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አድጎ የነበረው የመዲናይቱ ክለብ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ላይ ባስመዘገበው ውጤት በ2008 በአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ እየተመራ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አድጎ በመጣበት ዓመት ከሊጉ ለመሰናበት መሰናበቱ የሚታወስ ሲሆን ያለፉትን ሦስት የውድድር ዓመታት ደግሞ በከፍተኛ ሊግ ላይ ሲካፈል ቢቆይም ዳግም ወደ ሀገሪቱ ትልቁ ሊግ መመለስ አልቻለም፡፡

ክለቡ ባለፈው የውድድር ዓመት ከተጫዋቾች የደመወዝ ክፍያ ጋር በተያያዘ ቅሬታዎችን እያስተናገደ ዓመቱን የዘለቀ ሲሆን አሁንም የሦስት እስከ ሁለት ወራት ደሞዝ ክፍያን ለተጫዋቾች መፈፀም አልቻለም፡፡ ክለቡ በተጨማሪም እስካሁን ለ2012 የውድድር ዘመን በጀት እንዳልተመደበለት ሲነገር የአሰልጣኝም ቅጥር እና የተጫዋቾችን ግዢ ላይ ተሳትፎ እያደረገ እንዳልሆነ የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡

እንደ ስራ አስኪያጁ ገለፃ የከተማ አስተዳደሩ ክለቡ ይቀጥል ወይስ አይቀጥል ለሚሉ ጥያቄዎች መልሶችን ተነፍገዋል። “ይቀጥላል አይቀጥልም የሚል ምላሽን ከከንቲባ ፅህፈት ቤት አላገኘንም። የሚቀጥል ከሆነ ግን በጀት መመደብ አለበት። ከዚህ በፊት ከሐምሌ 1 ጀምሮ በጀት የሚመደብ ሲሆን እስካሁን ግን የተመደበልንም ነገር የሌለ ሲሆን እንደ ክለብ ይቀጥል የሚል መመርያ ልናገኝ አልቻልንም። እስከ አሁን ደብዳቤ እየተፃፃፍን ነው በግልፅ የማይቀጥል ከሆነ ንገሩን ብለን የመጨረሻ ደብዳቤም ፅፈንላቸዋል።” ብለዋል።

አቶ ገዛኸኝ ክለቡ ባለቤት አልባ በሚመስል መልኩ የፍላጎት ማጣት እንዳለ ያስረዳሉ “የፍላጎት ማጣት ይታያል። አዲስ አበባ ማለት ትልቅ ከተማ ነው። በጀት እናግኝ ከተባለ በተለያዩ መልኩ ከከተማው ህዝብም ሆነ ከከተማው አስተዳደር በበቂ መልኩ ማግኘት ይቻል ነበር። ይህን ለማድረግ ግን ፍላጎት የለም። የከተማ አስተዳደሩ ለዚህ ክለብ ትኩረት ከመስጠት ይልቅ በከተማው ላሉት ሌሎች ክለቦች ነው ድጋፉን የሚያደርገው።” ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ እግርኳስ ክለብ ከወንድ ቡድኑ በተጨማሪ የሴቶች፣ ከ20 ዓመት በታች እና ከ17 ዓመት በታች ቡድኖችን በስሩ የያዘ ክለብ ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ