ወልዋሎ ሁለት ተጫዋቾች አስፈረመ

በዝውውር መስኮቱ በስፋት ከተሳተፉት ክለቦች በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት ወልዋሎዎች የ የኤርሚያስ በለጠ እና አቼምፖንግ አሞስን ዝውውር ሲያጠናቅቁ የአብዱላዚዝ ኬይታን ውል አድሰዋል።

አማካዩ ኤርሚያስ በለጠ ባለፈው ዓመት ከአክሱም ከተማ ጋር ያሳለፈ ሲሆን ቀደም ብሎ ለኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ኢትዮጵያ ቡና ተጫውቷል። በ2007 ወደ የመን አቅንቶ ከአልሳቅር ጋር ሊጉን በሁለተኛነት ማጠናቀቅ የቻለው ኤርሚያስ ከየመን መልስ በአሰልጣኝ ድራገን ፓፓዲች አሰልጣኝነት ዘመን ለቡና መጫወቱ ይታወሳል።

ላለፉት ሁለት ዓመታት ከመቐለ ጋር ቆይታ ያደረገው ጋናዊው የመስመር ተከላካይ አቼምፖንግ አሞስ ለወልዋሎ ፊርማውን ያኖረ ሌላው ተጫዋች ነው። በሃገሩ ክለብ አሚዱስ የእግር ኳስ ህይወቱን የጀመረው ተከላካዩ ከዚህ በፊት በቦኸም እና ሪል ታሜሊ ሲጫወት በመቐለ የሁለት ዓመት ቆይታውም አንድ የተሳካ ዓመት አሳልፎ ባለፈው ዓመት በጉዳት ቡድኑ አላገለገለም። ከወልዋሎ ጋር ልምምድ ከጀመረ ሳምንት ያስቆጠረው ተከላካዩ ከአሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ጋር በድጋሜ የሚገናኘው ሲሆን እንደከዚህ ቀደም ሁሉ የአሰልጣኙ ቀዳሚ ምርጫ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

በሌላ ዜና ቢጫ ለባሾቹ የጊኒያዊው ግብጠባቂያቸው ዓብዱልአዚዝ ኬታን ውል ለተጨማሪ አንድ ዓመት አራዝመዋል። ባለፈው የውድድር ዓመት በዝውውር መስኮቱ መጨረሻ ቀናት ለረጅም ጊዜያት ከወሰደው ድርድር በኃላ የዛምቢያው ቢዩልድ ኮንን ለቆ ወልዋሎን የተቀላቀለው ግብጠባቂው በተጠናቀቀው ዓመት ቡድኑን በቋሚነት ማገልገሉ ይታወሳል።

በረከት አማረ ለኢትዮጵያ ቡና አሳልፈው የሰጡት ወልዋሎዎች ከዓብዱልዓዚዝ ኬታ በተጨማሪ ጀፋር ደሊል እና ወጣቱ ግብ ጠባቂ ሽሻይ መዝገቦ በአማራጭ ይዘው አዲሱ የውድድር ዘመን ይጀምራሉ።


© ሶከር ኢትዮጵያ