ከፍተኛ ሊግ | ነቀምት ከተማ በርካታ አዳዲስ ተጫዋቾች ወደ ቡድኑ ቀላቅሏል

ወደ ፕሪምየር ሊግ ለመግባት ተወሰኖለት ኋላ ላይ ውሳኔው ተቀልብሶ በከፍተኛ ሊግ እንደሚወዳደር ያረጋገጠው ነቀምት ከተማ ስድስት ተጫዋቾችን ሲያስፈርም አንድ ተጫዋች ከስር አሳድጓል።

ሰዒድ ግርማ ከፈረሙት መካከል ነው። በአማካይ ቦታ የሚጫወተው ሰዒድ በሀላባ ከተማ እና ሀምበሪቾ ተጫውቶ ያሳለፈ ሲሆን ዐምና በስልጤ ወራቤ በመጫወት አሳልፏል። ዘሪሁን ይልማ ሌላው አዲስ ፈራሚ ነው። ከዚህ ቀደም ለደቡብ ፖሊስ፣ ኢትዮጵያ ውሃ ስራዎች እና ቡታጅራ የተጫወተው ተከላካዩ ዐምና ሀላባ ከተማ ሲጫወት ቆይቷል።

አማካዩ ዝናቡ ባፋ ከሀዲያ ሆሳዕና ቡድኑን ተቀላቅሏል። ዝናቡ ከዚህ ቀድም ለደቡብ ፖሊስ፤ ድሬዳዎ ከተማ እና ጅማ አባጅፋር ተጫውቶ አሳልፏል።

የፊት መስመር ላይ ፀጋአብ ጌታቸው ከሲዳማ ቡና ሲፈርም የቀኝ መስመር ተጫዋቹ ቻላቸው መንበሩ ከደሴ ቡድኑን ተቀላቅሏል። ሌላው አጥቂ ኢብሳ በፍቃዱም ወደ ቀድሞ ክለቡ ተመልሷል። ከዚህ ቀደም ለነቀምት የተጫወተው ኢብሳ ሀዲያ ሆሳዕና እና አዲስ አበባ ከተማ ሌሎች የተጫወተባቸው ክለቦች ናቸው።

ከአዳዲስ ፈራሚዎች በተጨማሪ ወደ ዋናው ቡድን አንድ ተጨዋች ያደገ ሲሆን በግራ መስመር የሚጫወተው አብዲ ተሾመ የማደግ እድሉን ያገኘ ተጫዋች ሆኗል።

በተያያዘ ዜና የ17 ተጫዎቾችን ውል ያደሰው ክለቡ የዋና አሰልጣኙ ቾምቤ ገብረሕይወትን ውልም አራዝሟል። ከ2010 ጀምሮ ከቡድኑ ጋር የቆዩት አሰልጣኙ በቀጣዩ የውድድር ዘመንም በነቀምት ይቆያሉ።


© ሶከር ኢትዮጵያ