ኢንቨርቲንግ ዘ ፒራሚድ | ምዕራፍ ስምንት – ክፍል አራት

የጆናታን ዊልሰን Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics የአማርኛ ትርጉም የዛሬው መሠናዶ የስምንተኛው ምዕራፍ አራተኛ ክፍልን ይዞላችሁ ቀርቧል።


እንደ አብዛኞቹ አሰልጣኞች ሁሉ ስታን ኩሊስም በአሰልጣኝነት ዘመኑ የተከተለው የአጨዋወት ዘይቤ እርሱ ተጫዋች ሳለ ከሚተገብረው ጨዋታ ጋር እምብዛም የተገናኘ አልነበረም፡፡ ኩሊስ በተጫዋችነት ጊዜው ማጥቃትን የሚያዘወትር የመሃል-ተከላካይ አማካይ (Attack-Minded Centre-Half) ሆኖ ትልቅ ከበሬታን አትርፏል፡፡ ታላቁ ፌሬንክ ፑሽካሽም ” በተጫዋችነት ዘመኑ ምርጡ የመሃል-ተከላካይ አማካይ ነበር፡፡” ሲል ለኩሊስ ያለውን አድናቆት ገልጿል፡፡ የስታን ኩሊስ የመሪነት ብቃት ገና በለጋ ዕድሜው ተረጋግጧል፤ ተጫዋቹ በአስራ ዘጠኝ ዓመቱ ዎልቭስን፥ በሃያ ሁለት ዓመቱ ደግሞ እንግሊዝን በአምበልነት መምራት ችሏል፡፡ በአሰልጣኝነት ህይወቱ ስታን ከመጠን ያለፈ ጥንቁቅ እንደነበር ይነገራል፡፡ በተለይ በተጋጣሚ ቡድን የመሃል አጥቂዎች (Centre-Forwards) ዙሪያ ዘወትር ጥልቅና ዝርዝር ግምገማ ያካሂዳል፡፡ ሁሌም ከእጁ በማይለየው የግል አጀንዳው ላይ ያሰፈራቸውን ማስታወሻዎች ያገላበጠ ማንኛውም ሰው አሰልጣኙ ለጥቃቅን ጉዳዮች ሳይቀር ቀድሞ የመዘጋጀት ልማድ እንዳዳበረ በቀላሉ ይረዳል፡፡ ቶሚ ላውቶን አንድ አጥቂ እጅግ የተደራጀውን የኩሊስ ተከላካይ ክፍል ለማስከፈት ” ጥሶና በርድሶ የሚያሳልፍ የመድፈኛ ታንክ ኃይል እንዲሁም በእንግሊዝ የውሾች ውድድር ላይ የሚስተዋለው ከፍተኛ ፍጥነትና ስል እይታ” ሊኖረው እንደሚገባ ያስገነዘበውም ለዚህ ይመስላል፡፡

ኩሊስ በሌላ መለያ ባህርዩም ይመሰገናል፡፡ ፍርድ የማያጓድል፣ ፍትሃዊ ውሳኔ የሚያሳልፍ፣ ሥርዓት አክባሪና ወግ-አጥባቂ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ተጫዋች ሳለ ዎልቭሶች ከሊቨርፑል ጋር የሊጉን ዋንጫ ማረፊያ የሚወስን ፍልሚያ ያደርጋሉ፡፡ የመርሲሳይዱ ክለብ አጥቂ አልበርት ስተቢንስ ኩሊስን አልፎ ግብ ሊያስቆጥር ሲሄድ የያኔው የዎልቭስ የመሃል-ተከላካይ አማካይ ከኋላው ይጠልፈዋል፡፡ ኩሊስም ድርጊቱ ተገቢ እንዳልነበር በማመን ቡድኑ ላይ ቅጣት ምት ያሰጣል፡፡ ለዚህም ይመስላል ጆን አርሎት ” አክራሪ የመርህ ሰው!” ሲል የሚያወድሰው፡፡

ከአሰልጣኝነት የትምህርት ዝግጅቱ ጋር በተያያዘ ኩሊስ ከአፈንጋጩ የጦር ሻለቃ ፍራንክ በክሌይ ሥር መሰልጠኑ ከፍተኛ ጠቀሜታ ሳይሰጠው አልቀረም። በ1930ዎቹ ሻለቃ በክሌይ በውጤት ማጣት ሰበብ የሚፈጠር ማንኛውንም ትችት ለመጋፈጥ ወደኋላ የማይሉ እና ቡድናቸው ከባድ የሚባለውን የተጋጣሚ ጥቃት እንዲመክት የሚጥሩ ዝነኛ አሰልጣኝ ነበሩ፡፡ ፍራንክ በክሌይ ሞሊነክስ በሚገኘው መልበሻ ክፍል ውስጥ <Therapeutic Diathermy Machine> አስገጥመዋል፡፡ ማሽኑ ፈጣን ድግግሞሽ ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል ፍሰት (High-Frequency Electric Current) በመጠቀም ለሰውነት ህዋሳት ከፍተኛ ሙቀት ያመነጫል፤ ጡንቻዎችና መገጣጠሚያዎችን ከድካም በመታደግም ንቁ እንዲሆኑ ማድረግ ያስችላል፡፡ መሳሪያው በመላው ዓለም <Galvanism> በመባል ለሚታወቀውና ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ሞገድ ጨረሮችን በረቂቅ የሰውነት ክፍሎች ውስጥ በማስተላለፍ የዛሉ ጡንቻዎችን በማኮማተርና በማሳሳብ እንዲነቃቁ የሚረዱ የህክምና ምርመራዎችን (Sumsoidal and Faradic Treatments) የሚያካትት ነው፡፡ አሰልጣኙ ከ1939ኙ የእንግሊዝ እግርኳስ ማህበር ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ቀደም ብሎ ያለ ማንም አማካሪነት ከእንስሳት የሰውነት ክፍሎች የሚመነጩ (Animal Secretions) ምናልባትም ከዝንጀሮ እጢ የተወሰዱ እንደሆኑ የሚገመቱ ንጥረነገሮች ለተጫዋቾቹ በመርፌ እንዲሰጣቸው እስከማድረግ ደርሰዋል፡፡ ስታን ኩሊስ የያኔው የበክሌይ ውሳኔ አስመልክቶ መድሃኒቶቹ ለአካል ብቃት አልያም ለተክለ ሰውነት ግንባታ ቀጥተኛ የኃይል ሰጪነት ፋይዳ ባይኖራቸውም ሰዎች ሲጠቀሟቸው የተሻለ የሥነ-ልቦና ስሜት ላይ እንዲገኙ የሚያግዙ <Placebos> እንደነበሩ ያምናል፡፡

በወቅቱ ኩሊስ በእንግሊዝ እግርኳስ በሰፊዉ የተለመደው ቀጥተኛ የአጨዋወት ሥልት  (Orthodoxy) ላይ ጥያቄ አንስቶ በነጻነት የመሞገት ድፍረት አዳብሯል፡፡ አሳማኝና ጥልቅ ምላሽ ለማግኘትም ዳግም ወደኋላ ተመልሶ መሰረታዊውን ሥርዓት (Basics) ማጤን እንዳለበት አምኗል፡፡ ” ጠንክሮ መሥራትን ምንም ዓይነት ሌላ ተግባር ሊተካው አይችልም፡፡” የሚለው ንግግሩ የኩሊስ የዘወትር ውትወታ ነበር፡፡ ኩሊስ በእንግሊዝ እግርኳስ የአካል ብቃት ልምምድ ከፍተኛ ትኩረት እንዲቸረው በማድረግ ረገድ ከመጀመሪያዎቹ አሰልጣኞች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው፡፡ በቅድመ ውድድር ዘመን ተጫዋቾቹን ወደ ካኖክ ቼስ አውራጃ በመውሰድ በነፋሻማው አየር የሰውነት ማጎልበቻ፣ ብርታት ማሳደጊያና ጡንቻ ማፈርጠሚያ ሩጫዎችን (Stamina-Building Runs) ያስሮጣቸዋል፡፡ ከዚያ ቀደም ዓለም ዓቀፍ ውድድሮች ላይ በሯጭነት የተሳተፈውን ዝነኛ አትሌት ፍራንክ ሞሪስ የአካል ብቃት አሰልጣኝ ሆኖ እንዲሾም ያደረገውም ስታን ኩሊስ ነበር፡፡ ” ተጫዋቾቼ በቀላሉ የማይሸረሸር የቡድን መንፈስ እንዲጋባባቸው እፈልጋለሁ፤ በተክለ ሰውነትም ሆነ በአካል ብቃት ከማንም የላቁ መሆን አለባቸው፤ ተገቢውን የታክቲክ ትግበራ ሥርዓትም በሜዳ ላይ ማሳየት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህን ደግሞ በጠንካራ ሥልጠና እንዲያዳብሩት አደርጋለው፡፡” ይላል ስለ ከባድ ልምምዱ ጠቀሜታ ሲያስረዳ፡፡ በእርግጥ በአሰልጣኙ አማካኝነት እነዚያ ከአካል ብቃት ጋር በተጓዳኝ የሚሰጡት የታክቲክ ሥልጠናዎች በዋነኝነት በW-M (3-2-2-3) ፎርሜሽን ዙሪያ የሚያጠነጥኑት ስትራቴጂዎች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ በየጨዋታው በዋነኝነት ኳስን ወደፊት ለአጥቂዎች በቶሎ ማድረስ ቀዳሚ ዓላማው መሆኑም የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡

ተጫዋቾቻቸው ረብ-የለሽ ረዣዥም ቅብብሎች ሲከውኑ የሚውሉ በፍልስፍና የሚቀርቡት በርካታ አሰልጣኞች እንዳሉ ይከራከራል፡፡ እርሱ ግን ዘፈቀዳዊና እርባና ቢስ የቅብብል ሒደትን ፈጽሞ እንደማይፈቅድ አጥብቆ ይከራከራል፡፡ ሁሌም የቡድኑ ረዣዥም ኳሶች መርህና የመጨረሻ ግብ የተለየ ስለመሆኑ ማብራራት አይሰለቸውም።

የኩሊስ ዎልቭስ ተጫዋቾች በረዥም ርቀት የሚደረጉ ቅብብሎችን በፍጥነት ሁለቱ የመስመር አማካዮች (Wingers) ጂሚ ሙለን እና ጄሚ ሃኖክስ ጋር ማድረስ ተቀዳሚ ተግባራቸው ይሆናል፡፡ ” የተዛባ ግንዛቤ የሰረጸባቸው ጥቂት ተቺዎች የጨዋታ ዘዴያችንን ኳስን ወደፊት በመጠለዝ እና የተጋጣሚ ቡድን የመከላከል ክልል ውስጥ በፍጥነት ከመድረስ (Kick-And-Rush) ሥልት ጋር ያያይዙታል፡፡ የትኛውም አስተያየት እኛ ዘንድ ያለውን እውነታ ሊደብቅ አይችልም፡፡ በአጨዋወታችን ላይ እያንዳንዱ ሒደት በዕቅድና በምክንያት ይካሄዳል፡፡ ከተናጠል የተጫዋቾች እንቅስቃሴ ይልቅ ለቡድን ውህደት ቅድሚያ ብንሰጥም ኩሊስ የግል ቴክኒካዊ ብቃት ለነበራቸውና ለብቻቸው ተጽዕኖ መፍጠር ለሚችሉ ተጫዋቾች ፍጹም ፊት ነስቶ ወይም የእነርሱን ክህሎት ቸል ብሎ አያውቅም፡፡” ሲል የቡድኑ አምበልና የመሃል-ተከላካይ አማካዩ ቢሊ ራይት ኩሊስ በግል የተጫዋቾች ክህሎት ዙሪያ የነበረውን ለዘብተኛ አመለካከት ይናገራል፡፡

ፒተር ብሮድቤንት፣ ጂሚ ሙሬይና ቢሊ ማሰን የመሳሰሉትን ባለ ተሰጥኦ ተጫዋቾች በቡድኑ ቢያካትትም አሰልጣኙ ተሰጥዖ በመሰረታዊነት የቡድን ሥራ ግብዓት መሆን እንዳለበት ያምን ነበር፡፡ ኩሊስ ሚዛናዊ የመሆን የጸና አቋም ያለውን ጠቀሜታ በአግባቡ ቢረዳም ‘ትክክለኛው የአጨዋወት ሥርዓት’ የሚባለው አስተሳሰብ ግን ፈጽሞ የሚዋጥለት አልነበረም፡፡ ለኩሊስ የእግርኳስ ተቀዳሚ ግብ ማሸነፍ ነው፡፡

” ኳስ እግሩ ሥር የደረሰችለት እያንዳንዱ ተጫዋች ወዲያውኑ የማጥቃት ሒደቱን እንዲያስጀምር አዘወትረን ስለምንመክር የፊት መስመር ተሰላፊዎቻችን ችሎታቸውን የሚያሳዩበት ፋታ አያገኙም፡፡ ይህኛው የተናጠል የተጫዋቾች ክህሎት ምናልባት የተወሰኑ ደጋፊዎችን ሊያስደስት ይችል ይሆናል፤ ነገር ግን የቡድን እንቅስቃሴን የመገደብ የጎንዮሽ አሉታዊ ተጽዕኖ ስላለው ፈጣን የማጥቃት ሒደትን በማዳከም ዋጋ ያስከፍላል፡፡” ይላል ኩሊስ የሚታማበትን የጨዋታ አቀራረብ ሲያስረዳ፡፡

ብዙዎች ሃንጋሪ በዌምብሌይ እንግሊዝ ላይ በተቀዳጀችው የ6-3 ድል የታየውን የላቀ የቅብብል ሒደትና የተጫዋቾቹን ተፈጥሯዊ ችሎታ ሲያወድሱ ለኩሊስ ግን የእግርኳሳዊ እሳቤውን እርግጠኝነት ማመሳከሪያ ሆነለት፡፡ በታሪካዊው ጨዋታ የሃንጋሪው ግብ ጠባቂ ጊዩላ ግሮሲስ በተደጋጋሚ የእርሱን ክልል ከአደጋ ለመታደግ ኳስን በረዥሙ ለማራቅ ሲጥር እንዳስተዋለው ይመሰክራል፡፡ እንዲያውም ሃንጋሪዎች ካስቆጠሯቸው ስድስት ግቦች መካከል በራሳቸው የሜዳ ክፍል በተጀመረ እንቅስቃሴ የተመዘገበው አንዱ ብቻ እንደሆነም ይጠቅሳል፡፡ ሶስቱ ጎሎች አንድ ንክኪ ብቻ ባለው ረዥም ቅብብል፣ አንደኛው ጎል በሁለት ቅብብሎች፣ ሌላኛው ደግሞ ከቆመ ኳስ በቅጣት ምት የተገኙ ስለመሆናቸውም ይተነትናል፡፡ በዚያን ጊዜ እጅጉን የተወደደውና በአጭር ቅብብል ወደ ተጋጣሚ የሜዳ ክልል የሚደረስበት የአጨዋወት ሥልት (Pass-And-Move Football) የተስተዋለው ሃንጋሪዎች የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን ከእንግሊዞች በወሰዱበት የጨዋታው ሁለተኛ አጋማሽ ነበር፡፡

” በአንድ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሊፈጠሩ የሚችሉ የጎል እድሎች ቁጥር ኳሱ ከተጋጣሚ ቡድን የግብ ክልል ፊትለፊት ከሚገኝበት ድግግሞሽ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አልያም ተመጣጣኝነት (Direct Proportion) አለው፡፡ በዎልቭስ ቡድን የሚጫወቱ ተከላካዮች ኳስን ከአደጋ ክልል ለማራቅ (Clearance) ከዘገዩ ኳሱ በግብ ክልላችን ዙሪያ ለብዙ ደቂቃዎች የሚቆይበት አጋጣሚ ይፈጠራሉ፤ ለተጋጣሚ ቡድንም ጎሎች የማስቆጠር ዕድሎች ይመቻቹለታል፡፡ ከኋላ ኳስ መስርተን የራሳችንን የማጥቃት ሒደት ለማስጀመር  ብዙ ጊዜ የሚወስድብን ከሆነም ኳስ በተቃራኒ ቡድን የፍጹም ቅጣት ምት ወረዳ የሚንሸራሸርበት ጊዜ አናሳ ይሆንና ጎሎች የምናገኝባቸው እድሎች ይጠባሉ፡፡” በማለት የረዥም ቅብብሎችን አስፈላጊነት ያብራራል፡፡

ይቀጥላል...


ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡ ባለፉት አስራ ሦስት ዓመታትም አስር መፅሐፍትን ለህትመት አብቅቷል፡፡