የኢትዮጵያ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ የሚካሄድበት ቀን ታወቀ

የ2011 የኢትዮጵያ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ጥቅምት 23 እንደሚካሄድ ፌዴሬሽኑ ለክለቦቹ በላከው ደብዳቤ አስታውቋል፡፡

ከአዲሱ የውድድር ዘመን ጅማሮ በፊት የክለቦች የዋንጫ ዓይን መግለጫ ተደርጎ የሚቆጠረው ይህ ውድድር በ1977 ዓ.ም ጅማሮውን ሲያደርግ በተለያዩ ጊዜያት በወጣ ገባ መልኩ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ ባሳለፍነው ዓመት መጀመሪያ ላይ መከላከያን ከጅማ አባ ጅፋር ያገናኘው ጨዋታም በመከላከያ የበላይነት መጠናቀቁ ይታወሳል።

አዲስ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዐቢይ ኮሚቴ የሊጉ አዲሱ የውድድር ዘመን የሚጀምርበትን ቀን ይፋ ሲያደርግ ስለዚህ ውድድር የተባለ ነገር ባለመኖሩ እና በውይይቱም ጨዋታው ከግምት ባለመግባቱ የዘንድሮው የአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድር መካሄዱ ጥያቄ ውስጥ ቢገባም ፌዴሬሽኑ ዛሬ ለተሳታፊ ክለቦች በላከው ደብዳቤ ቀኑን ይፋ አድርጓል፡፡

በዚህም መሠረት የዘንድሮው ጨዋታ በዓምናው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ መቐለ 70 እንደርታ እና በኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊው ፋሲል ከነማ መካከል ጥቅምት 23 ቀን 2012 በአዲስ አበባ ስታዲየም 9:00 የሚደረግ ይሆናል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ