አዳማ ከተማ ዋንጫ በዚህ ወር ይካሄዳል

በአዳማ ከተማ እግር ኳስ ክለብ አስተናጋጅነት ከጥቅምት 22 ጀምሮ የአዳማ ከተማ ዋንጫ የቅድመ ዝግጅት የአቋም መፈተሻ ውድድር በከተማዋ ይካሄዳል፡፡

ውድድሩን የሚያስተናግደው ክለቡ ሲሆን ከረጅም አመት በኃላም ይህ ውድድር እንደተሰናዳ ለማወቅ ችለናል፡፡ ከ2005 በፊት በነበሩ አመታት ሲዘጋጅ እንደቆየ የተነገረው ይህ ውድድር ዳግም ከስምንት ዓመት በኃላ በደመቀ መልኩ ለማሰናዳት መዘጋጀቱን ሶከር ኢትዮጵያ ከክለቡ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡

በውድድሩ ላይ ራሱ አዳማ ከተማ ተሳታፊ የሚሆን ሲሆን የተስፋ ቡድኑም እንደሚካተት ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም ጅማ አባጅፋር፣ ድሬዳዋ ከተማ፣ ሀዲያ ሆሳዕና፣ ፋሲል ከነማ፣ ሲዳማ ቡና እና ሀዋሳ ከተማን ተካፋይ እንዲሆኑ ጥሪ የቀረበላቸው ሲሆን ፋሲል ከተማ ድሬዳዋ እና ጅማ አባጅፋር ማረጋገጫን ሰጥተዋል። ሌሎች ክለቦችም የክለቡን የተሳታፊነት ጥያቄ መቀበል ከቻሉ በድምሩ ስምንት ክለቦችን በማቀፍ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የሚካሄድ ይሆናል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ