ሰበታ ከተማ ሦስት የውጪ ዜጎች አስፈረመ

በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ እየተመሩ በርካታ ተጫዋቾችን እያዘዋወሩ የሚገኙት ሰበታ ከተማዎች አንድ ዩጋንዳዊ እና ሁለት ቡርኪናፋሷዊ ተጫዋቾችን አስፈርመዋል።

ሳቪዮ ካቡጎ ከፈረሙት መካከል ነው። ዩጋንዳዊው የ26 ዓመት ተከላካይ ለሀገሩ ክለቦች ቪክቶርያ ዩኒቨርሲቲ፣ ኬሲሲኤ፣ ዩአርኤ እና ቪላ የተጫወተ ሲሆን ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣቱ በፊት በኮንጎው ኤስ ሲ ቪታ ሲጫወት ቆይቷል። ተከላካዩ ለዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን በርካታ ጨዋታዎች ላይ ተሰለፈ ሲሆን በ2015 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ሀገሪቱ ወደ ውድድሩ እንድታመራ ያስቻለችውን ወሳኝ ጎል ጋና ላይ ማስቆጠሩ ይታወሳል።

ሲይላ ዓሊ ባድራ ሌላው አዲስ ፈራሚ ነው። ይህ ቡርኪናፋሷዊ የ26 ዓመት ተጫዋች የአጥቂ መስመር ተሰላፊ ሲሆን ለሀገሩ ክለቦች ዱጎዎላፊላ፣ ኤኤስ ሪል እና ለሞሮኮው ማስ ፌስ ክለቦች የተጫወተ ሲሆን ያለፉትን ሁለት ዓመታት በማሊው ስታደ ማሊየን አሳልፏል። ሲይላ ኢትዮጵያ በተሳተፈችበት የ2013 የአፍሪካ ዋንጫ የቡርኪናፋሶ ስብስብ አባል ነበር።


ሦስተኛው አዲስ ፈራሚ ባኑ ዲያዋራ ነው። ቡርኪፋሷዊው የአጥቂ መስመር ተጫዋች ለሀገሩ ክለብ ዲዮላሶ እና ለአልጄሪያው ጄኤስ ካቢሊ የተጫወተ ሲሆን ያለፈውን የውድድር ዓመት በሞሮኮው ኤኤስ ፋር አሳልፏል። 


© ሶከር ኢትዮጵያ