ቻን 2016፡ ሁለቱ የምዕራብ አፍሪካ ሃገራት ግማሽ ፍፃሜውን ተቀላቅለዋል 

በሩዋንዳ አዘጋጅነት እየተካሄደ ያለው የአፍሪካ ሃገራት ዋንጫ ቀጣይ ሁለት የሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች ዛሬ ተደርገዋል፡፡ የ2011 የቻን አሸናፊ ቱኒዚያን በማሊ 2-1 ተሸንፋ ከውድድሩ ስትሰናበት ጊኒ ዛምቢያን በመለያ ምት 5-4 አሸንፋ ፍፃሜ ግማሹን ተቀላቅላለች፡፡ 

ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሃገር ማሊ የካርቴጅ ንስሮቹን ከኃላ ተነስታ 2-1 ረታለች፡፡ ቱኒዚያ የቻን ዋንጫን ለሁለተኛ ግዜ የማሸነፍ የነበራት ፍላጎትም ሩብ ፍፃሜ ላይ ተገትቷል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ብልጫ የነበራት ቱኒዚያ በሲኤስ ሴፋክሲያን የመሃል አማካይ መሃመድ አሊ መንሱር የ14ኛ ደቂቃ ግብ አማካኝነት መምራት ችላ ነበር፡፡ ከዕረፍት መልስ ማሊዎች ተሽለው የታዩ ሲሆን በ71ኛው ደቂቃ አሊዮ ጀንግ በፍፁም ቅጣት ምት አቻ አድርጓል፡፡ አብዱላሂ ዲያራ ከ9 ደቂቃዎች በኃላ ማሊን ወደ ግማሽ ፍፃሜው የወሰደች ግብ አስቆጥሯል፡፡

image-a9cec0731f9ae8b34e27ad5079f7ef03090bb696d5d71f40fe116efc690edf99-V

ጊኒ ዛምቢያን በመለያ ምት አሸንፋለች፡፡ ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ በመሃል ዳኝነት በመራው የሁለቱ ብሄራዊ ቡድኖች ጨዋታ በመደበኛው እና በተጨማሪ 30 ደቂቃ 0-0 ጨዋታቸውን አጠናቅቀዋል፡፡ አላፊውን ቡድን በተሰጠው የመለያ ምት የጊኒው ግብ ጠባቂ አቡዱልአዚዝ ኬታ ሁለት ምቶችን አድኖ የጨዋታው ኮከብ ሁኗል፡፡ ከ14 የፍፁም ቅጣት ምቶችም ውስጥ አምስቱ ተስተዋል፡፡ ኬታ ጊኒ ናይጄሪያን 1-0 ባሸነፈችበት የምድብ ሶስት የመጨረሻ ጨዋታ ላይም አስገራሚ ብቃቱን ማሳየቱ ይታወሳል፡፡

የቻን ዋንጫን ከዚህ ቀደም የምዕራብ አፍሪካ ሃገራት አሸንፈው አያውቁም፡፡ ዘንድሮ ከአራቱ የፍፃሜ ግማሽ ተፋላሚዎች ውስጥ ሶስቱ የምዕራብ አፍሪካ ሃገራት መሆናቸው ለመጀመርያ ጊዜ ዋንጫውን የማንሳት ተስፋቸውን አጠንክሮላቸዋል፡፡

ማሊ በግማሽ ፍፃሜው ከኮትዲቯር ስትገናኝ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ከጊኒ ትጫወታለች፡፡ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎቹ በመጪው ረብዕ እና ሐሙስ ይካሄዳሉ፡፡

 

ረብዕ ጥር 25

11፡00 – ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ከ ጊኒ ሐሙስ ጥር 26

11፡00 – ኮትዲቯር ከ ማሊ

 

(ፎቶ – ካፍ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *