የኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ፕሪሚየር ሊግ 4ኛ ሳምንት ቅዳሜ እና እሁድ በተደረጉ ጨዋታዎች ቀጥሏል፡፡ ሀረር ሲቲ ወደ መሪነት ከፍ ሲል ንግድ ባንክ የሳምንቱን ከፍተኛ ውጤት አስመዝግቧል፡፡
ቅዳሜ በ08፡00 ሐረር ሲቲ ደደቢትን 2-1 አሸንፎ የደረጃ ሰንጠረዡን አናት ተቆናጧል፡፡ የሐረር ሲቲን የድል ግቦች ሚካኤል መኮንን እና ታድዮስ አዱኛ ከመረብ ሲያሳርፉ ዳዊት ደግአረገ የደደቢትን ግብ አስቆጥሯል፡፡ ውጤቱን ተከትሎ ሐረር ሲቲ በ8 ነጥብ 1ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ተሸናፊው ደደቢት ወደ 4ኛ ደረጃ አሽቆልቁሏል፡፡
በ10፡00 አዲስ አበባ ከተማ አፍሮ ፅዮንን በፉአድ ነስሩ ብቸኛ ግብ 1-0 አሸንፏል፡፡ የሰንጠረዡን ግርጌም ለአፍሮ ጽዮን አስረክቦ 1 ደረጃ አሻሽሏል፡፡
ትላንት ረፋድ በተደረገ ጨዋታ ኤሌክትሪክ ከ መከላከያ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይተዋል፡፡ የመከላከያን ግብ ዮሃንስ ደረጄ ሲያስቆጥር የኤሌክትሪክን ግብ ኢብራሂም ቢያኖ ከመረብ አሳርፏል፡፡ በእለቱ ግ ያስቆጠሩት ሁለቱም አጥቂዎች ዘንድሮ ጥሩ አቋም ላ የሚገኙ ሲሆን በተለይም ኤሌክትሪኩ ኢብራሂም የአጨራረስ ፣ ቦታ አያያዝ እና አካል ብቃት ወደፊት ጎልቶ መውጣት እደሚችል ያሳየ ነው፡፡
በ08፡00 የምንግዜም ተቀናቃኞቹ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ተገናኝተው በፈረሰኞቹ 2-1 አሸናፊን ተጠናቋል፡፡ እንደልቡ ደሴ እና ኪሩቤል በለጠ የቅዱስ ጊዮርጊስን ግቦች ሲያስቆጥሩ ታደለ መኮንን የቡናን ግብ አስቆጥሯል፡፡
በ10፡00 ንግድ ባንክ የሳምንቱን ከፍተኛ ግብ በማስመዝገብየኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚን 4-0 አሸንፏል፡፡ ሰለሞን ሙላው ኮከብ ሆኖ በዋለበት ጨዋታ ከ4ቱ ግቦች ሶስቱን በማስቆጠር ሐት-ትሪክ ሲሰራ በፍርዱ ተካልኝ ቀሪዋን አንድ ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡ ሰለሞን (ከላይ በምስሉ ላይ የሚታየው) በዘንድሮው ከ17 አመት በታች ፕሪሚየር ሊግ ሐት-ትሪክ የሰራ የመጀመርያው ተጫዋች ለመሆን በቅቷል፡፡
የደረጃ ሰንጠረዡ ከ4 ሳምንታት በኋላ ይህንን ይመስላል፡-
በደቡብ ዞን ሊካሄድ የነበረው የ5ኛ ሳምንት ጨዋታ ተማሪዎች የፈተና ወቅት ላይ በመሆናቸው ለሌላ ጊዜ ተሸጋግሯል፡፡