ሉሲዎቹ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ተካተቱ

 

የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን /ሉሲዎቹ/ የ2017 የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅታቸውን በቅርቡ ይጀምራሉ፡፡

የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌዴሬሽን /ካፍ/ የቶጎ ብሔራዊ ቡድን ከ2017 የአፍረካ እግር ኳስ ዋንጫ የማጣሪያ ውድድር በይፋ መውጣቱን ተከትሎ ባስተላላፈው ውሳኔ መሰረት የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታውን ከአልጄሪያ አቻው ጋር ከማርች 4 እስከ 20 /2016 ባሉት ቀናት ውስጥ ያካሂዳል፡፡ የመጀመሪያው ጨዋታ በአልጀርስ የሚከናወን ሲሆን የመልሱ ደግሞ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከሴቶች ብሔራዊ ቡድን ምዝገባ ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን የአሰራር ችግር መሰረት በማድረግ የሉሲዎቹ ተሳትፎ እንዲቀጥል ባደረገው ያላሰለሰ ጥረት በተለይም የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት በካይሮ የካፍ ዋና ጽህፈት ቤት እንዲሁም በርዋንዳ ኪጋሊ የቻን ውድድር ወቅት ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የካፍ የስራ ሃላፊዎች በማነጋጋር ያከነወኑት ዲፕሎማሲያዊ ተግባር የሚፈለገውን ውጤት አስገኝቷል፡፡

ኢትዮጵያ ለሴቶች እግር ኳስ ስፖርት እድገት ልዩ ትኩረት በመስጠት በአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች እና ከ20 ዓመት በታች ውድድሮች ያደረገችው ንቁ ተሳትፎና ብርቱ ተፎካካሪነት በካፍ ልዩ ስፍራ የተሰጠው መሆኑ ለተሳትፎው ቀጣይነት ከፍተኛ ድርሻ አበርክቷል፡፡

በእዚህ አጋጣሚ የካፍ ፕሬዚዳንት ሚ/ር ኢሳ ሀያቱ እንዲሁም ዋና ፀሃፊው ሂሻም ኤልማርኒ በተጫማሪም የካፍ የስራ አስፈጻሚ ኮሜቴ አባላት እና የስራ ሃላፊዎች ኢትዮጵያ በ2017 የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ውድድሮች እንድትካፈል ላደረጉት ከፍተኛ እገዛና ለተላለፈው ውሳኔ ፌዴሬሽኑ ታላቅ ምስጋናውን ያቀርባል፡፡ 

ውሳኔው በካፍ እና የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን መካካል የተፈጠረው መልካም ግንኙነት ውጤት ተደርጎ እንደሚወሰድም ፌዴሬሽኑ በጽኑ ያምናል፡፡

 

(ዜናው ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተላከ ነው)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *