አአ ከተማ ዋንጫ | ባህር ዳር ከተማ ድል አድርጓል

በ14ኛው የአዲስአበባ ከተማ ዋንጫ የመክፈቻ ጨዋታ ባህርዳር ከተማ በማማዱ ሲዲቤ ብቸኛ ግብ ወልቂጤን በመርታት የመጀመሪያውን ሶስት ነጥብ አሳክቷል፡፡

ተመጣጣኝ የሆነ እንቅስቃሴ በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ኳስን ለመቆጣጠር ጥረት ቢያደርጉም ውጤታማ መሆን ሳይችሉ በሚቆራረጡ የኳስ ቅብብሎች የተጀበ የመጀመሪያ 45 ደቂቃ አሳልፈዋል፡፡

እምብዛም በግብ ሙከራ ባልታጀበው በዚሁ አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች በመሀል ሜዳ ላይ በቁጥር በርከት ያሉ ቅብብሎችን ለማድረግ ቢሞክሩም ኳሶቹ ውጤታማ አልነበሩም፤ በመጀመሪያው አጋማሽ የተገኙት ሙከራዎች በአመዛኙ በመልሶ ማጥቃት የተገኙ ነበሩ በተለይም በባህርዳር ከተማ በኩል በ8ኛው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት የተገኘውን አጋጣሚ ፍፁም ዓለሙ ከሜንሳ ጋር ተገናኝቶ ያመከነው እንዲሁም በወልቂጢዎች በኩል ሄኖክ አወቀ ከባህርዳሮች የግብ ክልል ጠርዝ ላይ አልፎ ወደ ግብ የላከዎ ኳስ ለጥቂት ከግቡ አናት በላይ የወጣችበት ኳስ ተጠቃሽ ነበሩ፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተወሰነ መልኩ በተነቃቃ መንፈስ የጀመረ ይመስላል በተለይ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ባህርዳሮች የተሻለ ተጭነው መጫወት ችለዋል፡፡

በጨዋታውም በወልቂጤ ከተማዎች በኩል በቅርቡ አሰልጣኙኔ ተከትሎ ከኢኮስኮ የፈረመው የመስመር ተከላካዮ አቤነዘር ኦቴ በተደጋጋሚ የባህርዳር የግብ ክልል ውስጥ በመግባት ጥሩ ሞከራዎችን ሲያደርግ ተስተውሏል፡፡

የጨዋታው ብቸኛ ግብ በ74ኛው ደቂቃ የክለቡ አዲስ ፈራሚ ማማዱ ሲዲቤ በግንባር በመግጨት አስቆጥሯል፡፡

ከጨዋታውም መጠናቀቅ በኃላ የባህርዳር ከተማው አማካይ ፍፁም ዓለሙ የጨዋታው ኮከብ በመሆን የ10,000 ብር የዳሽን ባንክ ኩፖን ተሸላሚ ሆኗል።


© ሶከር ኢትዮጵያ