ሦስተኛው የኢቢሲ ስፖርት የሽልማት ሥነስርዓት ተካሄደ

በኢቢሲ የስፖርት ሽልማት በእግርኳስ ዘርፍ አማኑኤል ገብረሚካኤል እና ሴናፍ ዋቁማ አሸናፊ ሆነዋል።

ዛሬ አመሻሽ ላይ በስካይላይት ሆቴል የኢቢሲ ስፖርት ሽልማት ለሦስተኛ ጊዜ ተከናውኗል። ሽልማቱ ካካተታቸው አምስት ዘርፎች ውስጥም ሦስቱ እግር ኳስን የተመለከቱ ነበሩ። በዚህም በወንዶች እግር ኳስ ዘርፍ የመቐለ 70 እንደርታው አጥቂ አማኑኤል ገብረሚካኤል አሸናፊ መሆን ሲችል በሴቶች ደግሞ የአዳማ ከተማዋ ሴናፍ ዋቁማ ሽልማቱን በእጇ አስገብታለች።

ከሁለቱ ሽልማቶች በተጨማሪ በስፖርታዊ ጨዋነት ዘርፍ አምና ደቡብ ፖሊስን በዋና አሰልጣኝነት የመሩት አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ አሸንፈዋል። አሰልጣኙ ለዚህ ክብር የበቁት ዲላ ከተማን እያሰለጠኑ በነበርበት ወቅት ከወላይታ ሶዶ ጋር በነበራቸው ጨዋታ ቡድናቸው ግብ ቢያስቆጥርም ግቡ መረቡ በመቀደዱ ሳቢያ እንደተቆጠረ ለዳኞቹ በመናገር እንዲሻር በማድረጋቸው ነበር።


© ሶከር ኢትዮጵያ