ኢትዮጵያውያን ዳኞች ተጠባቂው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታን ይመራሉ

በአፍሪካ ውድድሮች ተሳትፏቸው እየጨመረ የመጣው ኢትዮጵያውያን ዳኞች በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ አልጀርያ ከ ዛምቢያ የሚያደርጉትን ተጠባቂ ጨዋታ ይመራሉ።

በምድብ 8 የሚገኙት ቡድኖች የሚያደርጉትን ይህን ጨዋታም በዋና ዳኝነት ባምላክ ተሰማ ፣ በረዳት ዳኝነት ክንዴ ሙሴ እና ትግል ግዛው ቴዎድሮስ ምትኩ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ይመሩታል።

በ2019 የአፍሪካ ዋንጫ ጠንካራ የተባሉ ጨዋታዎችን የመራው በአምላክ ተሰማ ያለፉትን ወራት አህጉራዊ ጨዋታዎች ላይ ሲዳኝ ያልተመለከትነው ሲሆን በአፍሪካ ዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ አልጄርያ ከ አይቮሪኮስት ያደረጉትን ጨዋታ ከመራ ወዲህ ለመጀመርያ ጊዜ አህጉራዊ ጨዋታ የሚመራ ይሆናል።

በማጣርያው ካሉት ምድቦች የተሻለ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ ምድብ የአፍሪካ ዋንጫው አሸናፊ አልጀርያ ፣ ጠንካራዋ ዛምቢያ ፣ ዚምባብዌ እና ቦትስዋናን የሚያገናኝ ሲሆን በመጀመርያው መርሃ ግብር አልጀርያን ከ ዛምቢያ በአልጀርስ እንዲሁም ዚምባብዌ ከ ቦትስዋና በሃራሬ ያገናኛል።

ከዳኝነት ጋር በተያያዘ ዜና ሞሮኮ በአፍሪካ ለመጀመርያ ጊዜ በምስል የታገዘ ዳኝነት (VAR) ለመተግበር ዝግጅቷን አጠናቃለች። ላለፉት ሳምንታት ቴክኖሎጂውን ለመተግበር በእንቅስቃሴ ላይ የቆየው የሞሮኮ ሮያል እግር ኳስ ፌደሬሽን ቀጣይ ሳምንት በጥሎ ማለፍ ግማሽ ፍፃሜ ታኒገር ከ ማራካሽ በሚያደርጉት ጨዋታ ቴክኖሎጂውን ተግባራዊ ያደርጋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ