የዝሆኖቹ ኮከብ ከማጣርያ ጨዋታዎች ውጭ ለመሆን ተቃርቧል

ዊልፍሬድ ዛሃ አይቮሪኮስት ከኢትዮጵያ እና ኒጀር  በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ላይ የመሰለፉ ነገር አጠራጥሯል።

በእንግሊዙ ክሪስታል ፓላስ የሚጫወተው ፈጣኑ የመስመር ተጫዋች ዊልፍሬድ ዛሃ ባለፈው ሳምንት ከቼልሲ ጋር በነበረው የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ባጋጠመው ጉዳት እስካሁን ድረስ የአይቮሪኮስት ብሄራዊ ቡድን ያልተቀላቀለ ሲሆን ጉዳቱም ከማጣርያ ጨዋታዎች ውጭ ሊያደርገው እንደሚችል እየተነገረ ይገኛል።

ተጫዋቹ ምንም እንኳ ቡድኑ በለንደን ደርቢ በተሸነፈበት ጨዋታ ሙሉ ዘጠና ደቂቃ ቢጫወትም ከጨዋታው በኃላ በእግሩ በረዶ አርጎ ታይቷል። የፓላሱ አሰልጣኝ ሮይ ሆጅሰንም ከጨዋታው በኃላ ዛሃ በጨዋታው ጉዳት እንዳስተናገደ ገልፀው የወሳኝ ተጫዋቻቸው ጉዳት ቀላል እንዲሆን ተመኝተዋል።

አሰልጣኝ ኢብራሂም ካማራ የፈጣኑ አማካይ ግልጋሎት የማያገኙ ከሆነ ከቻይና መልስ ከፓርማ ጋር ጥሩ ጊዜ እያሳለፈ ለሚገኘው ጀርቪንሆ ጥሪ ያደርጋሉ ተብሎ ይገመታል።


© ሶከር ኢትዮጵያ