የትግራይ ዋንጫ | ምዓም አናብስት ደደቢትን ረምርመዋል

ዛሬ ከተካሄዱት ሁለት የትግራይ ዋንጫ ጨዋታዎች አንዱ የሆነውና አስቀድመው ከምድብ መሠናበታቸውን ያረጋገጡት የደደቢትና መቐለ 70 እንደርታ ጨዋታ በመቐለ 5-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

የመቐለዎች ፍፁም ብልጫ በታየበት ጨዋታ ሰማያዊዎቹ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ደርሰው ሙከራ ያደረጉባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት ነበሩ። በጨዋታው ሙከራ ለማድረግ ቀዳሚ የነበሩት መቐለዎች ሲሆኑ ሙከራውም በኤፍሬም አሻሞ አማካኝነት የተደረገ ነበር። በአስራ ስድስተኛው ደቂቃም ያሬድ ከበደ ከሳሙኤል ሳሊሶ በጥሩ ሁኔታ የተሻገረለት ኳስ ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።

ከጎሉ በኃላም ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተደጋጋሚ ግዜ የደረሱት መቐለዎች በኤፍሬም አሻሞ አማካኝነት በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት ሁለት ግቦች አስቆጥረዋል። የመስመር አማካዩ የመጀመርያው ጎል ከግብ ጠባቂው የተተፋው ኳስ ተጠቅሞ ሲያገባ ሁለተኛው ግብ ከተከላካዮች አፈትልኮ በመውጣት ከግብ ጠባቂው አንድ ለአንድ ተገናኝቶ አስቆጥሯል።

ደደቢቶች በአጋማሹ በዓብዱልሐፊዝ ቶፊቅ እና ፉሴይኒ ኑሁ ተግባቦት ከፈጠሩት ሙከራ ውጭ ይህ ነው የሚባል ሙከራ ማድረግ አልቻሉም።

በሁለተኛው አጋማሽም የተሳካ የማጥቃት ጥምረት የነበራቸው መቐለዎች ግብ ለማስቆጠር ግዜ አልፈጀባቸውም። ሳሙኤል ሳሊሶ ከያሬድ ከበደ የተላከለትን ኳስ ወደ ግብነት በመቀየር ቡድኑ ጨዋታውን አራት ለባዶ እንዲመራ አስችሏል።

ከግቡ በኃላም ሙከራ ያልተለየው ጨዋታው በደደቢቶች በኩል በርከት ያለ ሙከራ አስተናግዷል። ከነዚህም ዮሐንስ ፀጋይ አሻምቶት አንቶንዮ አቡዋላ በግንባር ያደረገው ሙከራ ፣ ዮሐንስ ፀጋይ መቶ ቋሚው የመለሰበት ኳስ እና ፉሴይኒ ኑሁ ያደረገው ሙከራ ይጠቀሳሉ። በሰባ ሶስተኛው ደቂቃም አፍቅሮት ሰለሞን ከሳጥኑ ጠርዝ አክርሮ በመምታት ግሩም ግብ አስቆጥሮ የቡድኑን ብቸኛ ግብ አስቆጥሯል።

መደበኛ የጨዋታው ክፍለ ግዜ ተጠናቆ በተሰጠው ተጨማሪ ደቂቃ መቐለዎች ተቀይሮ በገባው ክብሮም አፅብሃ አንድ ተጨማሪ ግብ አክለው ጨዋታው አምስት ለአንድ ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎ መቐለ እና ደደቢት ከምድባቸው ሳያልፉ ቀርተዋል።

የጨዋታው ኮከብ የመቐለው የመስመር አማካይ ኤፍሬም አሻሞ በመሆን ተሸልሟል።


© ሶከር ኢትዮጵያ