የ2012 ፕሪምየር ሊግ የሚጀምርበት ቀን ሊራዘም ይችላል

ነገ የዕጣ ማውጣት ስነ-ሥርዓቱ የሚከናወነው የ2012 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሊራዘም የሚችልበት አጋጣሚዎች እየተፈጠሩ እንደሆነ መረጃዎች እየወጡ ይገኛል።

ፕሪምየር ሊጉን እንዲመሩ ሰባት አባላት ያሉት አዲስ የተዋቀረው ዐቢይ ኮሚቴ የዘንድሮ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኀዳር 13 እና 14 እንደሚጀመር ማሳወቁ ይታወቃል። ሆኖም ውድድሩ በሁለት መነሻ ምክንያቶች ሊራዘም እንደሚችል ቴውቋል።

የመጀመርያው ምክንያት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ከሁለት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታዎች መልስ እረፍት ሳያገኙ በቀጥታ ወደ ውድድር ማስገባት ይከብዳል በሚል ሲሆን ሁለተኛው በየክልሉ (የአዳማ ከተማ ፣ የትግራይ እና የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ) ውድድሮች እየተካሄዱ መሆኑና ውድድሮቹ ፍፃሜ የሚያገኙት ፕሪምየር ሊጉ በሚጀምር ወቅት በመሆኑ ነው።

በመሆኑም እነዚህን ሁኔታዎች ለማስታረቅ ሲባል ዐቢይ ኮሚቴው ዛሬ ቀትር ላይ ባደረገው መደበኛ ስብሰባ ሊጉን ለተወሰኑ ጊዜያት ለማራዘም ማሰቡን ሰምተናል። ይልቁኑም ነገ በአዳማ ከተማ ከጠዋቱ 03:00 ጀምሮ በኤክስኪዮቲቭ ሆቴል በሚደረገው የዕጣ ማውጣት ሥነ ስርዓት ላይ 16 የፕሪምየር ሊግ ክለቦች እንደ አጀንዳ ቀርቦ እንደሚወያዩበት ለማወቅ ችለናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ