ብርሃኑ ግዛው በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ሉሲዎቹን ይመራሉ

 

በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በተፈጠረው ስህተት ምክንያት ከ2016 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ውጪ ሆኖ የነበረው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን የቶጎ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ከማጣርያው ራሱን ማግለሉን ተከትሎ ወደ ማጣርያው ድልድል መመለሱን ፌዴሬሽኑ ዛሬ ጠዋት ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡

ፌዴሬሽኑ ለማጣርያው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን እንዲመራ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች ቡድን አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛውን የመረጠ ሲሆን የዳሽን ቢራ ሴቶች ቡድን አሰልጣኝ ቢንያም የብርሃኑ ምክትል ሆኖ ይሰራል ተብሏል፡፡ ሁለቱ አሰልጣኖች በቅርቡ ይደረጋል ተብሎ በተሰረዘው የኢጋድ ውድድር የኢትዮጵያን ከ18 አመት በታች ሴቶች ቡድን ተረክበው ዝግጅት ሲያደርጉ የነበሩ ናቸው፡፡

በየካቲት መጨረሻ ከአልጄርያ ጋር በአልጀርስ ለሚደረገው የመጀመርያ የማጣርያ ጨዋታ ለአለም ከ20 አመት በታች ውድድር ለማለፍ ከተቃረበው ስብስብ ፣ በቅርቡ ከማጣርያ ከተሰናበተው የ17 አመት በታች ቡድን ፣ ለኢጋድ ውድድር ተሰብስቦ ከነበረው ቡድንና በቀጣዩ ሳምንት ከሚጀመረው የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ተጫዋቾን መርጠው ወደ ዝግጅት እንደሚገቡ አሰልጣኝ ብርሃኑ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡

አሰልጣኙ ጨምረው እንደገለጹት ቡድኑን ከዚህ በፊት ማሰልጠናቸው እና ተጫዋቻቸውን በደንብ ማወቃቸው ጥሩ ቡድን ለመስራት እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *