ሪፖርት | ዋሊያዎቹ ዝሆኖቹን አጋደሙ

ለ2021 የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎችን እያደረጉ የሚገኙት ዋሊያዎቹ ኮትዲቯርን በሜዳቸው ከጨዋታ ብልጫ ጋር አሸንፈዋል።
ጨዋታውን ለመከታተል የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራን ጨምሮ በርከት ያሉ የፌደሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ አባላት በስታዲየሙ ተገኝተዋል። በጨዋታው ዋሊያዎቹ በመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን ሲፈጥሩ በተቃራኒው ኮትዲቯሮች ጨዋታውን መቆጣጠር ከብዷቸው ታይቷል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ከሦስት ቀናት በፊት አንታናናሪቮ ላይ ማዳጋስካርን ከገጠመው ቋሚ 11 ሁለት ለውጦችን አድርገዋል። በዚህም ጋቶች ፓኖምን በታፈሰ ሰለሞን እንዲሁም አማኑኤል ገ/ሚካኤልን በአዲስ ግዳይ ተክተው ለጨዋታው ቀርበዋል።

ጨዋታው እንደተጀመረ ኳስ መቆጣጠር የጀመሩት ዋሊያዎቹ በ3ኛው ደቂቃ ሳይታሰብ በተቆጠረባቸው ጎል መመራት ጀምረዋል። በዚህ ደቂቃ የተገኘውን የቅጣት ምት ኮትዲቯሮች ወደ ግብ መተውት የነበረ ሲሆን ኳሱን አቤል ማሞ እንደምንም ተፍቶ ኳሱን ከግብነት አስቀርቷል። ነገር ግን አቤል የተፋትን ኳስ የኮትዲቯሮች የቀኝ መስመር ተከላካይ እና አምበል ሰርጂ ኦሪየ አግኝቶት ኳስ እና መረብን አገናኝቷል። ሳይታሰብ ግብ ያስተናገዱት ዋሊያዎቹ የኳስ ቁጥጥራቸውን ፍጥነት በመጨመር ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል መድረስ ጀምረዋል። በዚህም በ10ኛው ደቂቃ የቡድኑ አምበል ሽመልስ በቀለ ከመሃል የተሰነጠቀለትን የአየር ላይ ኳስ በሚገባ ተቆጣጥሮ ግብ ለማስቆጠር የጣረ ሲሆን ተጨዋቹ የመታው ኳስ ቀላል በመሆኑ ግብ ጠባቂው ተቆጣጥሮታል።

አሁንም ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመሄድ ያልቦዘኑት ዋሊያዎቹ በ16ኛው ደቂቃ በተገኘ የቅጣት ምት አቻ ሆነዋል። አቡበከር ነስሩ ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የቅጣት ምት ሱራፌል ዳኛቸው ወደ ግብ መትቶ በተጨረፈ ኳስ የአቻነት ግብ ተቆጥሯል። ብሄራዊ ቡድኑ የአቻነት ግብ ካስቆጠረ በኋላም ተጨማሪ ግብ ተጋጣሚው ላይ ለማስቆጠር ጥረቶችን ቀጥሎ ሙከራዎችን አድርጓል። ለአብነት ያክል በ19ኛው ደቂቃ የመስመር ተከላካዩ አህመድ ረሺድ ለአዲስ ግዳይ አሻምቶለት አዲስ ያመከነው አጋጣሚ እጅግ ለግብ የቀረበ ነበር።

ጨዋታው ቀጥሎ በ25ኛው ደቂቃ ዋሊያዎቹ መሪ የሆኑበትን ኳስ ከመረብ አገናኝተው በስታዲየም የነበረውን ስሜት ዳግም አሟሙቀዋል። በዚህ ደቂቃ የቡድኑ አምበል ሽመልስ በቀለ በግል ጥረቱ ያገኘውን ኳስ እየገፋ ሄዶ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል።

ኮትዲቯሮች ሁለተኛውን ግብ ካስተናገዱ በኋላ በአንፃራዊነት በተሻለ ተጫውተዋል። ምንም እንኳን ቡድኑ ከመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በተሻለ ለመጫወት ቢሞክርም ግልፅ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ግን ሲቸገር ተስተውሏል። በተቃራኒው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች አጨዋወታቸውን ለዘብ አድርገው በመንቀሳቀስ ጨዋታውን ቀጥለዋል። የመጀመሪያው አጋማሽም ተጨማሪ ግብ ሳይስተናገድበት በዋሊያዎቹ መሪነት ተጠናቋል።


በሁለተኛው አጋማሽ ዋሊያዎቹ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተቃራኒ የኳስ ቅብብላቸውን ወደ ራሳቸው የግብ ክልል አድርገው ተንቀሳቅሰዋል። ዝሆኖቹ በበኩላቸው አጨዋታቸውን አሻሽለው ለመቅረብ ቢጥሩም እንደመጀመሪያው አጋማሽ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን መፍጠር ተስኗቸው ታይቷል።

የሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ሙከራ በ51ኛው ደቂቃ ተደርጓል። በዚህ ደቂቃ ታፈሰ ሰለሞን ለሽመልስ በቀለ ያቀበለውን ኳስ ሽመልስ ወደ ግብ ሞክሮት መረብ ላይ ሳያርፍ ቀርቷል። ተረጋግተው ጨዋታቸውን ሲጫወቱ የነበሩት ዋሊያዎቹ በ53ኛው ደቂቃ ሱራፌል ዳኛቸው የግብ ጠባቂውን አቋቋም ተመልክቶ ከርቀት በሞከረው ሙከራ ተጨማሪ ግብ ለማግባት ተቃርበው መክኖባቸዋል።


በጨዋታው ለጥቂት ደቂቃ መሪ የነበሩት ኮትዲቯሮች መልሰው መሪነታቸውን ለማግኘት የአጥቂ ተጨዋቾችን ቀይረው አስገብተዋል። አሰልጣኝ ኢብራሂም ካማራ ቀይረው ካስገቧቸው ተጨዋዋቾች ያኮ ሜቲ በአንፃራዊነት የተሻሉ ሙከራዎችን ሲያደርግ ታይቷል። ይህ ተጨዋች በ73ኛው ደቂቃ መሃል ለመሃል የተላከለትን ኳስ ተቆጣጥሮ አቤልን ቀይሮ የገባው ምንተስኖት አሎ መረብ ላይ ለማሳረፍ ሲጥር ተከላካዩ አስቻለው ታመነ እንደምንም አምክኖበታል።
ከጨዋታው የሚፈልጉትን ያገኙት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች አልፎ አልፎ በሚሰነዝሯቸው ፈጣን ሽግግሮች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጥረዋል። በዚህ የጨዋታ እንቅስቃሴም አዲስ ግዳይ ከታፈሰ ሰለሞን የተረከበውን ኳስ በጥሩ ሁኔታ ወደ ግብ መቶ የቡድኑን መሪነት ከፍ ለማድረግ ቢሞክርም ሳይሳካለት ቀርቷል። ከዚህ ሙከራ በተጨማሪ ቡድን ተቀይሮ በገባው ደስታ ደሙ አማካይነት ሌላ ሙከራ አድርጎ ነበር።


ኮትዲቯሮች በመጨረሻዎቹ 10 ደቂቃዎች ይበልጥ ተጭነው ተጫውተዋል። በዚህም በ80ኛው ደቂቃ ኒኮላስ ፔፔ ከመስመር የተረከበውን ኳስ እየገፋ ገብቶ የሞከረው እና ኢላማውን የሳተበት እንዲሁም በ87ኛው ደቂቃ ፔፔ በድጋሜ ከቅጣት ምት የተመታውን ኳስ አግኝቶ የሞከረው ነገር ግን የቡድን አጋሩ ያወጣበት ሙከራዎች ተጠቃሽ ናቸው። ሙሉ 90 ደቂቃዉ ተጠናቆ በጭማሪ ሰዓት ኮትዲቯሮች በያኮ ሜቲ የግንባር ኳስ የጨዋታው የመጨረሻ ሙከራ አድርገዋል።
ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳያስተናግድ በዋሊያዎቹ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ድሉን ተከትሎ የባህር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም በአህጉራዊ የነጥብ ውድድሮች ሽንፈት ሳያስተናግድ መጓዙን ቀጥሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ