አአ ከተማ ዋንጫ | ሰበታ ከተማ የምድብ ሁለት የበላይ ሆኖ አጠናቀቀ

በምድብ ሁለት የመጨረሻ የጨዋታ ዕለት በ8 ሰዓት ወልዋሎን ከሰበታ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ ተሻሽለው የገቡት ሰበታ ከተማዎች በማሸነፍ የምድባቸው የበላይ ሆነው ግማሽ ፍፃሜውን መቀላቀል ችለዋል።

ወልዋሎዎች በኢትዮጵያ ቡና ከተረታው ስብስብ ውስጥ የአንድ ተጫዋች ብቻ ለውጥ ሲያደርጉ በአንጻሩ ሰበታዎች የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገው ወደ ጨዋታው ገብተዋል።

ለተመልካች እጅግ አሰልቺ በነበረው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታ እጅግ ደካማ የሆነ እንቅስቃሴ በሁለቱም ቡድኖች ተስተውሏል። በአንፃራዊነት በመልሶ ማጥቃት የተሻሉ የነበሩት ወልዋሎዎች በመጀመሪያው አጋማሽ በሶስት አጋጣሚዎች ከተከላካዮች ጀርባ በረጃጅሙ በሚጣሉ ኳሶች አደጋ ለመፍጠር ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፤ ምንም እንኳን ኳሶቹ በደካማ ውሳኔ አሰጣጥ ውጤታማ ባይሆኑም። በተጨማሪም በዚሁ አጋማሽ በ30ኛው ደቂቃ ሳሙኤል ዮሐንስ ከሳጥን ውጭ በቀጥታ አክርሮ የመታውና ለጥቂት የግቡን አግዳሚ ታካ የወጣችው ኳስ የአጋማሹ ተጠቃሽ ሙከራ ነበረች።

ሰበታዎች ምንም አይነት የግብ ሙከራ ማድረግ ባልቻሉበት የመጀመሪያ አጋማሽ ወልዋሎዎች በኩል ኳስ በሚያጡበት ወቅት በመስመሮች መካከል እጅግ ሰፋፊ ክፍተቶች ቢኖሩም በሰበታ ከተማዎች በኩል ይህን ለመጠቀም የተደረገ ጥረት አለመኖሩ አግራሞትን ያጫረ ሁኔታ ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ ፍፁም ተሻሽለው የገቡት ሰበታ ከተማዎች በሁለተኛው አጋማሽ ይበልጥ ሁለቱ የመስመር ተከላካዩችን ወደፊት በማስጠጋት በሜዳው ስፋት ለጥጠው እንዲጫወቱ በማድረግ ወልዋሎዎችን የመከላከል አደረጃጀት በቀላሉ ሲያስከፍቱ ተስተወሏል። በ52ኛው ደቂቃም ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ጃዋር ባኑ ዲያዋራ ለሰበታ ቀዳሚዋን ግብ ሲያስቆጥር በተመሳሳይ በደቂቃዎች ልዩነት ከጌቱ ኃይለማርያም የተሻማውን ኳስ ተጠቅሞ ሳሙኤል ታዬ የቡድኑን ሁለተኛ ግብ አስቆጥሯል።

ከግቧ መቆጠር በኋላ ሰበታዎች በተደጋጋሚ ጥሩ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን ቢፈጥሩም መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል።


ወልዋሎዎች በ63ኛው ደቂቃ ሠመረ ሃፍታይን ቀይረው ወደ ሜዳ ካስገቡ በኃላ ጫና ፈጥረው ለመጫወት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶም በ78ኛው ደቂቃ ጁሊየስ ናንጂቡ ባስቆጠረው ግብ ወደ ጨዋታው ቢመለሱም ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።

ጨዋታው በሰበታ ከተማዎች የ2ለ1 የበላይነት መጠናቀቁን ተከትሎ ሰበታ ከተማ በ7 ነጥብ የምድብ ሁለት የበላይ ሆኖ ማጠናቀቅ ችሏል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ሰበታ ከተማዎች በሁለተኛ አጋማሽ ላሳዩት መነቃቃት ዓይነተኛ ሚና የነበረው ጌቱ ኃይለማርያም የጨዋታው ኮከብ በመሆን ተመርጧል።


© ሶከር ኢትዮጵያ