የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 8ኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሃ ግብር በሆነው በዚህ ጨዋታ መከላከያ ድሬዳዋ ከተማን በአዲስ አበባ ስታድየም 11፡30 ላይ ያስተናግዳል፡፡
የአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ መከላከያ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ወት አቋም ማሳየት አልቻለም፡፡ የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊው በውድድር ዘመኑ መጀመርያ ከነበረው አስደናቂ ብቃት ቀስ በቀስ መንሸራተት እሳየ እንደመሆኑ የ1 ወር እረፍቱ ክፍተቶቹን ለመድፈን ይጠቅመዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከሳምንት በኋላ በካፍ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ክግብፁ ምስር አል-ማቃሳ ጋር የሚጫወተው መከላከያ የነገውን ጨዋታ በድል መወጣት የአሸናፊነት ስነልቦናቸውን ያሳድግላቸዋል፡፡
በነገው ጨዋታ ከመከላከያ በኩል ምንም የተጫዋች ጉዳት የሌለ ሲሆን ለረጅም ጊዜ በጉዳት ከሜዳ የራቀው ጀማል ታሰው ለጨዋታ ብቁ ሆኗል፡፡ አጥቂው መሃመድ ናስርም ከጉዳቱ በማገገሙ ነገ በመጀመርያ አሰላለፍ ይካተታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የመሰረት ማኒ ድሬዳዋ ከተማ ሊጉ ከመቋረጡ በፊት የመጨረሻዎቹን 3 ጨዋታዎች በማሸነፍ ደረጃውን በከፍተኛ ደረጃ ማሻሻል ችሏል፡፡ አዳዲስ ተጫዋቾችን ከቡድኑ ጋር የማዋሃጃ እና የቅድመ ውድድር ዘመን ዝግጅት ጊዜ ለማግኘት ያልታደሉት መሰረት ማኒ አሁን ቡድናቸውን ለማዘጋጀት በቂ ጊዜ በማግኘታቸው ይበልጥ የተሸሻለ ቡድን ልንመለከት እችላለን፡፡
በነገው ጨዋታ በእጁ ላይ ጉዳት የደረሰበት ሲሳይ ደምሴ የቀድሞ ክለቡን ለመግጠም ወደ ሜዳ የማይገባ ሲሆን ቀላል ጉዳት አጋጥሞት የነበረው ዳዊት እስጢፋኖስ ከጉዳቱ አገግሞ የነገውን ጨዋታ ለማድረግ ብቁ ሆኗል፡፡
ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም
መከላከያ ፡ ተሸነፈ – አቻ – አቻ – አሸነፈ – ተሸነፈ
ድሬዳዋ ከተማ ፡ ተሸነፈ – ተሸነፈ – አሸነፈ – አሸነፈ – አሸነፈ
የእርስ በእርስ ግንኙነቶች
ድሬዳዋ ከተማ ወደ ሊጉ ካደገበት 2001 እስከ ወረደበት 2004 ድረስ ሁለቱ ቡድኖች ባደረጓቸው 8 ጨዋታዎች መከላከያ 6 ጨዋታ በድል በመወጣት ድሬዳዋ ላይ የበላይነቱን ይዟል፡፡