ሀዲያ ሆሳዕና የስታዲየም ማሻሻያ ግንባታውን አጠናቋል

ሀዲያ ሆሳዕና በዘንድሮ ውድድር ዓመት ለሚወዳደርበት ፕሪምየር ሊግ የሚጫወትበትን ሜዳ የማሻሻል ሥራ ማጠናቀቅ ችሏል።

በ1976 አገልግሎት መስጠት የጀመረው የአቢዮ ኤርሳሞ መታሰቢያ ስታዲየም ለወራት የማስፋፊያ እና ዕድሳት ሲደረግለት ቆይቶ ሥራውን በፍጥነት አጠናቋል። ተመልካቹን ከተጫዋቾች የሚለየው አጥር ተሰርቶ ሲጠናቀቅ የስታዲየሙ መቀመጫ መጠነኛ እድሳት ተደርጎለታል። የመጫወቻ ሜዳውም ለጨዋታ ዝግጁ እንዲሆን የተደረገ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ የጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል እና የቪድዮ መቅረጫ ቦታ በተመሳሳይ መልኩ አዘጋጅቷል

የፕሪምየር ሊጉ ዐቢይ ኮሚቴ የሜዳውን ጥራት እና ጨዋታ ለማጫወት ያለውን ዝግጁነት አወዳዳሪው አካል ከገመገመ በኋላ ሆሳዕና በሜዳው የሚያደርጋቸውን ጨዋታ እንዲያከናውን ማረጋገጫ ሰጥቶታል። በዚህም መሠረት ነብሮቹ የ2012 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመክፈቻ ጨዋታውን ከመቐለ ከሜዳው ውጪ ከተጫወተ በኋላ በሜዳው እና በደጋፊው ፊት ከሀዋሳ ከተማ ጋር ኅዳር መጨረሻ ላይ እንደሚያደርግ ታውቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ