ሳላዲን ሰዒድ ስለ ወቅታዊ አቋሙ ይናገራል

ትናንት በተጠናቀቀው የ14ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ጎልተው ከወጡ ተጫዋቾች መካከል አንጋፋው አጥቂ ሳላዲን ሰዒድ አንዱ ነው። ከረዥም ጊዜ ጓዳት በኋላ ወደ ሜዳ በመመለስ ጥሩ ብቃቱን ያሳየው ሳላዲን በአራት ጎል የውድድሩ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ በመሆን አጠናቋል። ሶከር ኢትዮጵያም ወቅታዊ አቋሙ ዙርያ አጭር ቆይታ አድርጋ እንዲህ አቅርበነዋል።

ውድድሩን እንዴት አገኘኸው?

በጣም አስደሳች ውድድር ነበር። በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የነበረው ፉክክር፣ የደጋፊዎች ስርዓት ያለው አደጋገፍ፣ አዘጋጆቹ ውድድሩ እንዲያምር ያደረጉት ጥረት ከዚህ በፊት ከነበረው ሲቲ ካፕ የዘንድሮው የተለየ በጣም ደስ የሚል ነበር።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ለኹለት ዓመታት ከዋንጫ ርቆ ቆይቶ ነበር። በዚህ ውድድር አሸናፊ ሆኖ ማጠናቀቁ በቡድኑ ላይ የሚፈጥረው በራስ መተማመን እና ቡድኑ ራሱን ለማየት ያደረገው ጥረት ተሳክቷል ማለት ይቻላል?

አዎ። ዋናው ወደ ዚህ ውድድር የገባንበት አላማችን ይሄ ነበር። የከተማ ዋንጫ ማሸነፋችን ለፕሪሚየር ሊጉ ለምናደርገው ጉዞ ትልቅ መነሳሳትን ይፈጥራል። ከዋንጫ እንደመራቃችን አሸናፊ ሆነን ማጠናቀቃችን ጠቀሜታው የጎላ ነው። ቡድኑ በሜዳ ላይ እንዳያችሁት ከጨዋታ ጨዋታ ራሱን እያስተካከለ እየተደራጀ መጥቷል። ወደ ፕሪምየር ሊጉ ስንገባም ይህን ጥንካሬያችንን ይዘን የምንዘልቅ ይሆናል።

በከተማው ዋንጫ ላይ ዳግም ተወልደሀል ማለት ይቻላል። ተቀይረህ ገብተህም በመጀመርያም ተሰላፊ በመሆን ጎሎችን በማስቆጠር የውድድሩ ኮከብ ጎል አስቆጣሪ ሆነህ ማጠናቀቅህ ችለሀል። በጉዳት ከሜዳ ርቀህ መተህ እንዲህ ያለ ጥንካሬ ማሳየትህ ሚስጢሩ ምድነው ትላለህ?

አንድ ተጫዋች ራሱን ለሁሉም ነገር ማዘጋጀት አለበት። ወደ እግርኳሱ ስትገባ በሀገር ውስጥም ሆነ ውጭም ስትጫወት ራስህን ለማንኛውም ነገር ማዘጋጀት ይመስለኛል ተጫዋቹን ፕሮፌሽናል የሚያስብለው። ያንን ለማሟላት ደግሞ እግርኳሱ የሚፈልገውን ነገር በተቻለኝ አቅም ለመተግበር የማደርገው ስራ ውጤታማ ያደረገኝ።

ለብሔራዊ ቡድን ዳግመኛ መጠራት ምን ዓይነት ስሜት ፈጠረብህ?

ሜዳ ላይ በግልህም እንደ ቡድንም የምታደርገው እንቅስቃሴ ነው ለብሔራዊ ቡድን ጥሪ እንዲቀርብልኝ ያደረገው። አሰልጣኞቹም በዚህ መመዘኛ መሠረት እንደጠሩኝ የማስበው። ሁሉጊዜም ራሴን ለጨዋታ ዝግጁ አድርጌ መቅረብ እፈልጋለው። አሁንም በብሔራዊ ቡድንም ሆነ በክለቤ ስኬታማ ሆኜ የውድድር ዓመቱን ማጠናቀቅ የምችለው የጤንነቴ ሁኔታ አስተማማኝ ሲሆን ነው። ያው እንደሚታወቀው ጉዳት ተደራርቦብኝ የምፈልገውን ነገር ማድረግ እንዳልችል አድርጎኛል። አሁን ውስጤ ትልቁን ቦታ የሚሰጠው ጤነኛ ሆኜ ከፈጣሪ ጋር ጠንክሬ ክለቤንም ሀገሬንም ማገልገል ነው ።

አሁን የጉዳት ሁኔታ እንዴት ነው? መሻሻሎች እያሳየ ይገኛል?

ያው የጉዳቴ ዓይነት የተለያየ ነው። ጉልበቴን አሞኝ ረጅም ጊዜ የቆየ ቀዶ ጥገና አድርጌ ከሜዳ መራቄ ይታወሳል። ከጉልበት ጉዳቴ አገግሜ ወደ ሜዳ ተመልሼ ጥሩ ጊዜ እያሳለፍኩ የቁርጭምጭሚት ጉዳት አስተናገድኩ። እንደገና ደግሞ ሳላስበው ከሜዳ ውጭ ያለ ህመም የትርፍ አንጀት አጋጥመኝ። በህክምና ስህተት ሁለቴ ቀዶ ጥገና አደረኩ። ይህ ነው የምትለው አይደለም ጉዳቴ የተለያየ ነው። አሁን ባለው ነገር ደስተኛ ነኝ። ስለ ቀጣዩ ፈጣሪ ያውቃል።


© ሶከር ኢትዮጵያ