የአአ ከተማ ዋንጫ መጠናቀቅ ዙርያ መግለጫ ተሰጠ

የ14ኛውን የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ መጠናቀቅ አስመልክቶ የአአ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከአአ ስፖርት ኮሚሽን በጋራ በመሆን በጊዮን ሆቴል ዛሬ ቀትር ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

በመግለጫው ላይ የአአ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አረጋይ፣ የአአ ግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት ኃይለየሱስ ፍስሐ እና የሥራ አስፈፃሚ አባል የኔነህ በቀለ የተገኙ ሲሆን የ14ኛው የአአ ከተማ ዋንጫ በስኬት መጠናቀቁን የፌዴሬሽኑ ፕሬዝደን ዝርዝር መግለጫ ሰጥተዋል።

የመግለጫው ዋና ዋና ሀሳቦች የሚከተሉት ናቸው፡-

” የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያሰናዳው 14ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ እጅግ በተሳካና አላማውን በጠበቀ መልኩ ከጥቅምት 29 – ህዳር 14/2012 ዓም በአዲስ አበባ ስታዲየም ሲከናወን ቆይቶ በከፍተኛ ድምቀት ተጠናቋል፤ ይህ እንዲሆን ፌዴሬሽናችን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገርና በቅንጅት መስራቱ አይነተኛ አስተዋፅኦን አበርክቷል፤ ይህ ውድድር ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በፊት የሚከናወንና ቡድኖች ለአቋም መለኪያነት የሚጠቀሙበት፣ ፌዴሬሽናችን ዓመታዊ እቅዱን ለማከናወን ገቢ የሚያገኝበት ብቻ ሳይሆን የስፖርት ቤተሰቡም በጉጉት ጠበቆ ከወራት በኋላ በሜዳ የተገናኘበት እንደመሆኑ እጅግ ሰላማዊ ብቻ ሳይሆን ለሀገራችን የሠላም ተምሳሌትና ከወትሮው የተለዩ መልካም ግኑኝነቶች የሚንፀባረቅበት እንዲሆን አስቀድመን ሰፊ ስራዎች ሰርተናል።

” ከእዚህም መካከል፤ ከተሳታፊ ቡድኖች አመራሮች ጋር በውድድሩ ደንብና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ተደጋጋሚ የምክክር መድረኮችን በማዘጋጀት ተወያይተናል፤ የደጋፊ ማህበራት አመራሮች ጋር በመነጋገርና በስራቸው ያሉ ስቴዋርዶች በስፖርታዊ ጨዋነት ዙሪያ የግንዛቤ ማስጫበጫ መድረክ በማመቻቸት ስለውድድሩ ሠላም ግምባር ቀደም ሚና እንዲኖራቸው ተደርጓል።

” በስታዲየሙ ከትኬት መቁረጥ ጀምሮ ያሉ መጉላላቶች ለማስቀረት ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በኦንላን ሲስተም ለማከናወን ያቀድነው ተሳክቶ ከአሞሌ ሽያጩ በቀዳሚነት እንዲከናወን በማድረግ በድርጅቱ በኩል የተሸጡ ቲኬቶች ብዛት – 107,021 (በመቶኛ 62%)ሆነዋል።

” ውድድድሩን በኢትዮጵያ የውስጥ ሙሉ ጨዋታው በአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ በሬዲዮና ቴሌቪዥን በቀጥታ ስርጭት በመተላለፉ ስታዲየም መግባት ላልቻሉና በመላው ዓለም ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ባሉበት ሆነው ሊመለከቱ ችለዋል።

” የሁሉም ጨዋታዎችን የጨዋታ ቁጥራዊ መረጃዎችን (አናሊስስ) ከሚሰራው ኢትዮ ፉትቦል ሶሉሽን ጋር ግኑኝነት ፈጥረን በመስራታችን በያንዳንዱ ጨዋታ የቡድናቸውን አቋም እንዲያውቁ መረጃዎችን እዲሁም የጨዋታውን ሙሉ ፊልም እየሰጠን እንገኛለን፡፡

” በቅርብ ቀን ከደጋፊዎች በ8833 የመረጡትንና የባለሙያዎችን ውሳኔ መሠረት በማድረግ የውድድሩን ኮከብ ተጫዋች ሽልማትና የክለቦች ድርሻን በማስመልከት የምስጋና ፕሮግራም ቀንን በቅርቡ ይፋ እናደርጋለን።

” ፌዴሬሽናችን የአቀዳቸው ስራዎች በስኬት ተጠነቋል ብለን እናምናለን ከገቢም አኳያ ካቀድነው 80 በመቶ ያሳካን ሲሆን ከባለፈው አመት ገቢ 180 በመቶ ሆኖልናል ፡፡

‘ ” ከእጣ ማውጣት ጀምሮ እስከውድድሩ መጠናቀቅ ድረስ ላስመዘገብናቸው ድሎችና ስኬቶች ከፍተኛ ድርሻ ለነበራቸው አካላት ላበረከቱ ተቋማት እና ግለሰቦችን እናመሰግናለን።”

በመጨረሻም ከጋዜጠኞች ለቀረቡ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ምላሽ በመስጠት ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ