የቀድሞ የአውስትራሊያ ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን አጥቂ ቴድሮስ አለማው ያቢዮ የሆላንድ ሶስተኛ ዲቪዚዮን ክለብ ውል ቢያቀርብለትም ሳይቀበል መቅረቱን ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግሯል፡፡
ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የመጫወት ፍላጎት እንዳለው የሚናገረው ቴድሮስ በሳለፍነው የጥቅምት እና ህዳር ወር በጀርመን እና ሆላንድ በሚገኙ ክለቦች የሙከራ ጊዜ አሳልፏል፡፡ ቴድሮስ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደሰጠው አስተያየት ከሆነ የቀረበለት ውል ማራኪ አይደለም፡፡ “ጥሩ የሙከራ ግዜያትን አሳልፊያለው፡፡ የሆላንድ ሶስተኛ ዲቪዚዮን ክለብ ውል አቅርበውልኝ ነበር፡፡ ነገር ግን ውሉ ለእኔ የሚመች አልሆነም፡፡ ስለሆነም ወደ ሜልቦርን አውስትራሊያ ተመልሼ የቀድሞ ክለቤን ተቀላቅያለው፡፡” ብሏል፡፡
ቴድሮስ በኤንፒኤል ቪክቶሪያ ሊግ ለሚወዳደረው ሴንት አልባን ሴንትስ ይጫወታል፡፡ የህግ ተማሪ የሆነው ተጫዋቹ ከዚህ ቀደም ለአውስትራሊያ የኤ ሊግ ክለብ ሜልቦርን ቪክትሪ ተጫወቷል፡፡