ቅድመ ዳሰሳ | ስሑል ሽረ ከ ኢትዮጵያ ቡና

በነገው ዕለት ከሚደረጉት ሁለት ጨዋታዎች አንዱ የሆነውና በትግራይ ስቴድየም የሚካሄደውን ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

የመጀመርያው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ነገ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ሲጠናቀቁ ስሑል ሽረዎች ኢትዮጵያ ቡናን የሚያስተናግዱበት ጨዋታ በሁለቱም ቡድን ደጋፊዎች ተጠባቂ ነው።

በዝውውሩ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ በትግራይ ክልል ዋንጫ የተሳተፉት ስሑል ሽረዎች በውድድሩ አጀማመር ብዙ ክፍተቶች ያሉበት ቡድን ይዘው ቢጀምሩም በጊዜ ሂደት መሻሻሎች በማሳየታቸው በነገው የሊጉ መጀመርያ ጨዋታ ቀላል ግምት አይሰጣቸውም።

ሽረዎች በቅድመ ውድድር በርካታ የአማካይ ተጫዋቾቻቸው በጉዳት በማጣታቸው በአብዛኛው በመስመር ላይ የተንጠለጠለ የማጥቃት አጨዋወት የነበራቸው ሲሆን አማካዮቹ አክሊሉ ዋለልኝ እና ሙሉዓለም ረጋሳ ከጉዳት መልስ ማግኘታቸው በአማካይ ክፍል ላይ የተወሰነ ለውጥ ያደርጋሉ ተብሎ ሲጠበቅ ቡድኑ በመከላከል ላይ ያለው መሰረታዊ ችግሮች መቅረፍ ግድ ይለዋል።

ሽረዎች በጨዋታው በቅጣት እና በጉዳት የሚያጡት ተጫዋች የለም።

በአዲስ አሰልጣኝ እና በአዲስ የጨዋታ አቀራረብ ወደ ውድድር የገቡት ኢትዮጵያ ቡናዎች በአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ስር የመጀመርያ የነጥብ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ቡናማዎቹ በአዲስ አበባ ዋንጫ ላይ በኳስ አመሰራረት ሂደት እና በማጥቃት ሽግግር ጨምሮ የተወሰኑ ችግሮች የተስተዋሉበት ሲሆን በዚህ ጨዋታ ላይም ወሳኝ ተጫዋቾቻቸው ቢያጡም ከተጋጣሚያቸው ጥንካሬ አንፃር  ብዙ ፈተናዎች ይገጥማቸዋል ተብሎ አይጠበቅም። ሆኖም ስሑል ሽረዎች አጨዋወታቸው ላይ ተጭኖ የመጫወት አቅም የሚያላብሱ ከሆነ ኢትዮጵያ ቡናዎች በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ አንዳንድ ጨዋታዎች ላይ እንደታየው ሊቸገሩ እንደሚችሉ ይገመታል።

ቡናማዎቹ በነገው ጨዋታ ወንድሜነህ ደረጄ ፣ አቡበከር ናስር እና አማኑኤል ዮሐንስን በጉዳት አያገኙም።

እርስ በእርስ ግነኙነት

ሁለቱ ቡድኖች ስሑል ሽረ ሊጉን በተቀላቀለበት የ2011 ውድድር ዓመት ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች በየሜዳቸው የ1-0 ድሎችን አሳክተዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ስሑል ሽረ (4-2-3-1)

ምንተስኖት አሎ

ዓብዱሰላም አማን – በረከት ተሰማ – አደም ማሳላቺ – ረመዳን የሱፍ

አክሊሉ ዋለልኝ – ሙሉዓለም ረጋሳ

መድሃኔ ብርሃኔ – ያስር ሙገርዋ – ዲድየ ለብሪ

ሳሊፍ ፎፋና

ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)

በረከት አማረ

አህመድ ረሺድ – ፈቱዲን ጀማል – ኢብራሂም ባጃ – አሥራት ቱንጆ

ዓለምአንተ ካሣ – ፍቅረየሱስ ተ/ብርሀን – ታፈሰ ሰለሞን

ሚኪያስ መኮንን – እንዳለ ደባልቄ – አላዛር ሽመልስ


© ሶከር ኢትዮጵያ