ሪፖርት | ተጠባቂው ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል

የ2012 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመርያ ጨዋታ አዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ባለሜዳዎቹ አዳማዎችን ከፋሲል ከነማ ያገናኘው ጨዋታ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
ኢንተርናሽናል ዳኛ ባዓምላክ ተሰማ በመራው ጨዋታ ባለሜዳዎቹ አዳማዎች የፋሲል ከነማን ፍፁም ያልተደራጀ አጨዋት እና መዳከም በመጠቀም ወደ ጎል መቅረብ የጀመሩት ገና 2ኛው ደቂቃ ነበር። በጥሩ ቅብብል ሳጥን ውስጥ በመግባት በፋሲል ተከላካዮች ተደርቦ የተመለሰውን ኳስ ቡልቻ ሹራ በጥሩ ሁኔታ አግኝቶ ከሳጥን ውጭ አጥብቆ ወደ ጎል የመታውን የዐፄዎቹ ግብጠባቂ ሳማኬ ሚኬል ወደ ውጭ ያወጣበት የባለሜዳዎቹ የመጀመርያ ሙከራ ነበር።

ከሁለት ደቂቃ በኃላ ከመሐል ሜዳ ጅማሮውን ያደረገ ኳስ ከነዓን ማርክነህ እና ዳዋ ሆቴሳ አንድ ሁለት ተቀባለው ከሳጥን ውጭ ዳዋ አክርሮ ቢመታውም ለጥቂት በግቡ አናት ወጥቶበታል። በፋሲሎች ላይ የወሰዱትን የማጥቃት የበላይነት አጠናክረው የቀጠሉት ባለሜዳዎቹ አዳማዎች ለማመን የሚከብድ የጎል አጋጣሚ አምክነዋል። በ8ኛው ደቂቃ በግራ ጠርዝ የተሰጠውን ቅጣት ምት ዳዋ ሆቴሳ የመታውን ግብጠባቂው ሳማኬ ሲተፋው ፉአድ ፈረጃ ነፃ የማግባት አጋጣሚ አግኝቶ አገባው ሲባል ያመከነው ኳስ የሚያስቆጭ ነበር።

እንግዶቹ ፋሲሎች ለወትሮ ከሚታወቁበት እንቅስቃሴ ወርደው ሲታዩ በመልሶ ማጥቃት ወደ አዳማ የሜዳ ክፍል ይግቡ እንጂ የአዳማን ተከላካዮች ሰብሮ መግባት ሲሳናቸው ከሳጥን ውጭ ኢላማውን ያልጠበቀ ሙከራዎችን ሲያደርጉም ተስተውሏል።

የአዳማ የበላይነት በቀጠለው በዚህ ጨዋታ ከማዕዘን ምት የተሻገረውን ተከላካዮ ቴዎድሮስ በቀለ ጥሩ አጋጣሚ አግኝቶ በግራ እግሩ ቢነታውም ግብጠባቂው ሳማኬ በቀላሉ ኳሱን የያዘበት ሌላ ለአዳማዎች ጎል መሆን የሚችል ዕድል ነበር።

ከዚህ በኃላ ያለው የጨዋታ እንቅስቃሴ በነበረው ፍጥነት ሳይቀጥል እየቀዘቀዘ ሄዶ ምንም አይነት የጎል ሙከራ ሳንበልከት 36ኛው ደቂቃ ላይ ደርሷል። ቡልቻ ሹራ ከመሐል ሜዳ የተሻገረለትን ኳስ ከግብጠባቂው ሳማኬ ጋር ብቻውን ተገናኝቶ ሆኖም ግብጠባቂን አልፎ ለማግባት በማሰቡ የተጨናግፈበት የግብ ዕድል አዳማን መሪ ማድረግ የሚቸል ሌላ የሚያስቆጭ አጋጣሚ ሆኖ አልፏል።

ከእረፍት መልስ የተቀዛቀዘው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በ57ኛው ደቂቃ አማኑኤል ጎበና እና ከነዓን ማርክነህ በጥሩ ጥምረት ተቀባብለው የፈጠሩት የጎል አጋጣሚ ወደ ጎልነት አይቀየር እንጂ የኳሱ ፍሰት እና ሂደት ለተመልካች አስደሳች ነበር።

የተወሰደባቸውን የመሐል ሜዳ ብልጫ ለመቆጣጠር አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ሱራፌል ዳኛቸውን በመቀየር ሐብታሙ ተከስተን በማስገባት ያደረጉት ጥረት ወደ ኃላ ተስበው ካልሆነ በቀር ወደ ፊት በመሔድ ለማጥቃት የነበራቸው ድርሻ ብዙም ሳይለወጥ ቀርቷል። በዚህም እንደመጀመርያው አጋማሽ ሁሉ አሁንም ፋሲሎች በመልሶ ማጥቃት የጎል ዕድሎችን መፍጠር ላይ አተኩረዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ምንም አንኳ አጥቂውን ሚካኤል ጆርጅን ወደ መጨረሻዎቹ ደቂቃ ቢያስገቡም አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የጥንቃቄ አጨዋወት በመምረጣቸው ተስፋዬ ነጋሽ እና እስማኤል ሳንጋሪን በማስገባት ፉአድ ፈረጃ እና ዳዋ ሆቴሳ መቀየራቸው በመጀመርያው አጋማሽ ከነበራቸው የተሻለ የማግባት አጋጣሚ በመቀነስ በቀሩት ደቂቃዎች ብዙም የጎል ዕድሎችን ሳይፈጥሩ ወጥተዋል።

ተዳክመው የመጡት ዐፄዎቹ ግልፅ የማግባት አጋጣሚ ለመፍጠር ቢቸገሩም 78ኛው ደቂቃ ከሳጥን ውጭ ሙጂብ ቃሲም አክሮ የመታውን ኳስ ስራ ፈቶ የዋለው የአዳማው ግብጠባቂ ጃኮ ፔንዜ በቀላሉ ይዞበታል። በጨዋታውም የተለየ ነገር ሳይፈጠር የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ጨዋታቸውን ያደረጉት አዳማ ከተማ እና ፋሲል ከነማ ያለ ጎል በአቻ ውጤት አጠናቀዋል።

በመጨረሻም የተፃፈውን የዳኝነት ህግ ለማስከበር ኢተርናሽናል ዳኛ በዓምላክ ተሰማ በየጨዋታው እንቅስቃሴ ይወስዳቸው የነበሩ እርምጃዎች በቀጣይ በየትኛውም ሜዳ ዳኞች ሁሉ ሊተገብሩት የሚገባው ጥሩ ጅማሮ ሲሆን በሁለቱም ደጋፊዎች መካከል በፍፁም ስፖርታዊ ጨዋነት ክለባቸውን ብቻ ደግፈው የወጡበትም መንገድ የጨዋታው መልካም ገፅታ ነበር።


© ሶከር ኢትዮጵያ