የአሰልጣኞች አስተያየት | ሰበታ ከተማ 1-3 ወልዋሎ

በአንደኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ወልዋሎ ከሜዳው ውጭ ሰበታ ከተማን 3ለ1 በመርታት ሥስት ነጥብ አሳክቷል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላም የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።


“ክፍተቶችን ቀርፈን ለመምጣት ከፍተኛ ጥረት አድርገናል” አብርሃ ተዓረ – የወልዋሎ ምክትል አሰልጣኝ

” ጨዋታው ጥሩ የሚባል ነበር። በተለይ ለእኛ የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ በጣም ጠቅሞናል፤ ዛሬ ከሰበታ ከተማ ጋር ስንጫወት ለሦስተኛ ጊዜ ነው። በውድድሩ የነበሩብን ክፍተቶች ቀርፈን ለመምጣት ከፍተኛ ጥረት አድርገናል፤ ይህም ውጤታማ አድርጎናል። በየሳምንቱ ዝግጅት የምናደርገው ለአንድ ጨዋታ ነው። ስለዚህ በዛሬው ውጤት ሳንዘናጋ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንሰራለን።”

“በመልሶ ማጥቃት የሚመጡ ኳሶችን በመቆጣጠር ረገድ ችግሮች ነበሩብን” ውበቱ አባተ – ሰበታ ከተማ

“ኳስ በመቆጣጠሩ ረገድ ብዙ ችግር አልነበረብንም፤ በመልሶ ማጥቃት የሚመጡ ኳሶችን በመቆጣጠር ረገድ ግን ችግሮች ነበሩብን። በሁለቱም አጋማሾች ኳሶቻችን ወደፊት ሲሄዱ በፍጥነት ይባክኑ ነበር። የውድድር ዘመኑ ገና ማራቶን ነው፤ የዛሬው የመጀመሪያ ጨዋታ ነው ክፍተቶች እንዳሉ ተመልክተናል። ጎሎች በቀላል ስህተቶች እያስተናገድን እንገኛለን፤ ይህ መታረም ይኖርበታል። በዛሬው ጨዋታ ከመኖርያ ፍቃድ በተያያዘ ቡድኑን ያላገለገሉ ተጫዋቾች ሲመለሱ ነገሮች የተሻሉ ይሆናል።”


© ሶከር ኢትዮጵያ