የአሰልጣኞች አስተያየት | ወላይታ ድቻ 2-0 ሲዳማ ቡና

ከመጀመርያው ሳምንት ተጠባቂ ጨዋታዎች መካከል የነበረው የወላይታ ድቻ እና ሲዳማ ቡና በባለሜዳዎቹ አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኋላ አሰልጣኞቹ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

” እውነት እንነጋገር ከተባለ ሜዳው ምቹ አይደለም” ገብረክርስቶስ ቢራራ – ወላይታ ድቻ

ስለጨዋታው

” ከጨዋታው በላይ ስፖርታዊ ጨዋነቱ አስደስቶኛል፤ ይሄ ለኔ በልጦብኛል። እኛ ሦስት ነጥብ ማግኘቱ አይደለም በዋናነት ያሳሰበን። ከዚህ በፊት በሁለቱም ቡድኖች ላይ የሚወሩ መጥፎ ነገሮች ስለነበሩ ያን አስቀርቶ እናንተም እንዳያችሁት በስፖርታዊ ጨዋነት በሰላም በመደረጉ እኔ በጣም ደስተኛ ነኝ። የመጀመሪያ ጨዋታ እንደመሆኑ ተጫዋቾቼ ያሳዩት ነገር መልካም ነው ፤ ገና ግን ብዙ ይቀረናል። ወደ ትክክለኛው መንገድ እስኪመጡ ግፋ ቢል አራት እና አምስት ጨዋታ ያስፈልጋል። ያኔ ነው የኛን ተጫዋቾች መለካት የምንችለው። አሁን ባገኘነው ውጤት ግን ደስተኛ ነኝ፡፡ በእርግጥ ሙሉ አይደለንም። እውነት እንነጋገር ከተባለ ሜዳው ምቹ አይደለም። ሜዳችን ምቹ ቢሆን ከዚህ በላይ መሆን እንችል ነበር፡፡ ኳስ የሚችሉ ልጆች አሉ በሌሎች ሜዳዎች ከዚህ በተሻለ እንሰራለን ብዬ አምናለሁ፡፡ ”

” በሜዳው በጣም በጣም ቅር ተሰኝቻለሁ ” አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ – ሲዳማ ቡና

ስለ ጨዋታው

” ጨዋታው ጥሩ እና ስፖርታዊ ጨዋነት የታየበት ነው፡፡ በሁለቱም በኩል ደጋፊ ላደረገው መልካም ነገር አመሰግናለሁ። ከዛ ውጪ ወደ ጨዋታው ስመለስ ለኛ አስቸጋሪ ጨዋታ ነበር። ምክንያቱም ለኛ አጨዋወት ሜዳው ፍፁም ምቹ አልነበረም። ያለን አማራጭ ረጃጅም ኳሶችን መጫወት ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ለተቃራኒ ቡድን ምቹ ነው። ሲዳማ ቡና ከተጀመረ ጀምሮ እንደዚህ ተጫውቶ አያውቅም። ለዚህ ደግሞ ሜዳው ነው ያስገደደን። ኳሱን ይዘን መጫወት አልቻልንም ፤ እነሱም ይዘው ተጫውተው አይደለም። እኛ የሰራናቸውን ስህተቶች ነው የተጠቀሙት። እንደኔ ማራኪ ኳስ የታየበት ነው ብዬ አላምንም። በሜዳው በጣም በጣም ቅር ተሰኝቻለሁ። ምክንያቱም እግር ኳስ የሚታይበት ሜዳ አይደለም መስተካከል አለበት፡፡”

የሁለተኛ አጋማሽ የሚካኤል እና የዳዊት ቅያሪ ኳስን ለመቆጣጠር ያለመ ስላለመሆኑ

“መስሎ ሊሆን ይችላል እንጂ እንደዛ አይደለም። ምክንያቱም እነሱ ካገቡ በኃላ ወደ ኃላ ሸሹ። ለዛ ነው ሚካኤል እና ዳዊት ዕድሉን ያገኙት እንጂ የመጫወቻ ሜዳ አልነበረንም። የኛ ቡድን ያገኘውን ረጃጅም ኳሶች መስመር ላይ ነበር የሚጥለው ፤ እነሱም በተመሳሳይ። ስለዚህም መሀል ላይ ኳስ ይዘን ለመጫወት ተቸግረናል። ተጫዋቼ ይዘው የሚጫወቱ ናቸው ለመቆጣጠር ስለማይመች ብቻ ነው ብልጫ የተወሰደብን የመሰለው እንጂ እነሱም ኳሱን አንሸራሽረው አይደለም። ግን በደንብ ሜዳውን የተረዱት ይመስለኛል፡፡ ከዛ ውጪ መሀል ላይ ለመጫወት ተቸግረናል፡፡ ”

በጨዋታው በርካታ ኳሶችን ስላመከነው ግብ ጠባቂው መሳይ አያኖ

” እውነት ነው ! በጣም በጣም ብዙ ኳሶችን አድኗል። ግን ኳሶቹ በተደጋጋሚ ይሞከሩ የነበረው ሜዳው በሚያሰራን ስህተት ነው። እንደውም እሱ ብዙ ኳስ ባያድን ኖሮ ጥሩ ነገር አይኖርም ነበር። ከዛ ውጪ በተጫዋቾቼ ምንም የምፈርደው የለም። ግብ ጠባቂያችን መሳይ በግል ላደረገው ጥረት በዚህ አጋጣሚ ሳላደንቀው አላልፍም፡፡ ”


© ሶከር ኢትዮጵያ