ሪፖርት | መቐለዎች የዐምና ድላቸውን የማስከበር ጉዟቸውን በድል ጀምረዋል

ምዓም አናብስት በያሬድ ከበደ እና አማኑኤል ገ/ሚካኤል ግቦች ሀዲያ ሆሳዕናን በማሸነፍ የውድድር ዓመቱን በድል ከፍተዋል።

ጨዋታው በዝግ መካሄዱን ተከትሎ ከተለመደው የትግራይ ስታዲየም ድባብ በተለየ መንገድ የተካሄደው የዛሬው ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ አሰልቺ እንቅስቃሴ የታየበት ነበር።

ጨዋታውን በሦስት ተከላካዮች ወደ 3-5-2 የሚጠጋ አደራደር ይዘው የገቡት ሀዲያዎች በአጋማሹ በአመዛኙ በአምስት ተከላካዮች መጫወታቸው በመከላከሉ ላይ ጥሩ ቢንቀሳቀሱም በማጥቃቱ ላይ ግን ይህ ነው የሚባል ዕድል መፍጠር አልቻሉም። ሆኖም ቡድኑ በተለይም ጫና በፈጠረባቸው የመጨረሻ ደቂቃዎች ሙከራዎች አድርገዋል ፤ ከነዚህም ቢስማርን አፒያ ከቢስማርክ ኦፖንግ የተላከለትን ኳስ ተጠቅሞ ያመከነው ወርቃማ ዕድል እና አፈወርቅ ኃይሉ የሞከረው ይጠቀሳሉ።

የተጋጣምያቸው የመከላከል አደረጃጀት አልፈው ንፁህ ዕድሎች ለመፍጠር የተቸገሩት መቐለዎችም ጥቂት የማይባሉ ዕድሎች ፈጥረዋል። ከነዚህም አማኑኤል ገ/ሚካኤል ከሳሙኤል ሳሊሶ የተሻገለት ኳስ ተጠቅሞ ያደረገው ሙከራ እና ያሬድ ከበደ በግምባሩ ገጭቶ ታሪኬ ጌትነት በድንቅ ብቃት ያዳነው ኳስ ይጠቀሳሉ። አስናቀ ሞገስ ከርቀት አክርሮ መቶ ያደረገው ጥሩ ሙከራም ሌላ የሚጠቀስ ሙከራ ነው።

ጥቂት የግብ ሙከራዎች እና ተቀራራቢ ፉክክር የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ በአስር ደቂቃ ውስጥ ሦስት ግቦች ያስመለከተን ነበር።

በአጋማሹ ሙከራ ለማድረግ ቀዳሚ የነበሩት ሀድያዎች ነበሩ። ቢስማርክ አፖንግ ከሩቅ አክርሮ መትቶ ያደረገው ሙከራ እና ቢስማርክ አፕያ ተጫዋቾች አታሎ ገብቶ በደካማ ውሳኔ አሰጣጥ ችግር ያመከነው ወርቃማ ዕድል በሀድያ በኩል ከታዩት ሙከራዎች የተሻሉ ነበሩ።

በሃምሳ ሦስተኛው ደቂቃ ያሬድ ከበደ ከአማኑኤል ገብረሚካኤል የተሻገረለትን ኳስ በመቆጣጠር ተከላካይ አልፎ ግብ በማስቆጠር ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። ከደቂቃዎች በኃላም አማኑኤል ገብረሚካኤል በረጅሙ የተላከለትን ኳስ ከተከላካዮች አምልጦ በመቆጣር ወደ ጎልነት ለውጦ የቡድኑን መሪነት ወደ ኹለት ከፍ ማድረግ ችሏል።

ከግቡ በኋላ አጨዋወታቸው እና አደራደራቸው በመለወጥ ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉት ነብሮቹ በቢስማርክ አፒያ ጥሩ ሙከራ ሲያደርጉ በሃምሳ ስምንተኛው ደቂቃም በደስታ ጊቻሞ አማካኝነት ግብ አስቆጥረዋል። ተከላካዩ ከቅጣት ምት የተሻማው ኳስ ተከላካዮች ተረባርባው ካወጡት በኃላ ነበር በግምባሩ ግቡን ያስቆጠረው።

ከግቦቹ መቆጠር በኃላ ከጥሩ ፉክክር ውጭ ይህ ነው የሚባል ሙከራ ያልታየበት ጨዋታው በባለሜዳዎቹ ሁለት ለአንድ አሸናፊነት ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ