ጅማ አባ ጅፋር ቀጣይ ጨዋታውንም ከሜዳው ውጪ ያደርጋል

ከዐምናው ተሻጋሪ ቅጣት እየተፈፀመበት የሚገኘው ጅማ አባ ጅፋር የሊጉ ሦስተኛ ሳምንት ጨዋታውን ከሜዳው ውጭ እንደሚያደርግ ታውቋል።

ባሳለፍነው ዓመት በ26ኛው ሳምንት ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር በነበረው ጨዋታ በተፈጠረ የዲሲፕሊን ጥሰት ኹለት ጨዋታ ከሜዳ ውጭ እንዲጫወት ቅጣት ተላልፎበት ለዘንድሮ ዓመት ቅጣቱ ተሻጋሪ ሆኖበት እየተፈፀመበት ይገኛል።

የቅጣቱ መጀመርያን ትናንት በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ከባህር ዳር ከተማ ጋር ተጫውቶ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ጨዋታውን መጠናቀቁ ይታወሳል። በሁለተኛ ሳምንት እሁድ ኀዳር 28 ቀን በአዲስ አበባ ስታዲየም ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ይጫወት እና በሦስተኛ ሳምንት ቅዳሜ ታኀሳስ 4 ቀን ከሲዳማ ቡና ጋር በሜዳው በመጫወት ሲገባው ቀሪ ቅጣቱ ምክንያት በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም የሚጫወት መሆኑ ታውቋል።

ከትናንትናው ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላም አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ይህን አረጋግጠዋል። አባጅፋሮች ዘንድሮ በሜዳቸውና በደጋፊያቸው ፊት በአምስተኛ ሳምንት ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስን በመግጠም የሚጀምሩ ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ