ሲዳማ ቡና የሁለተኛ ሳምንት ጨዋታውን በዝግ ያደርጋል

በ2011 የውድድር ዘመን በተፈጠረ የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ቅጣት ተላልፎበት የነበረው ሲዳማ ቡና ዐምና ቅጣቱ ያልተፈፀመ በመሆኑ በዚህ ሳምንት ስሑል ሽረን ሲገጥም ተግባራዊ ይሆናል፡፡

ሲዳማ ቡና እና ደቡብ ፖሊስ ግንቦት 17 ቀን 2011 ባደረጉት የ26ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ሲዳማ ቡና 4ለ2 መርታቱ ይታወሳል፡፡ በጨዋታው 64ኛው ደቂቃ ላይ ደቡብ ፖሊስ 2ለ1 የሚመራበትን ግብ ካስቆጠረ በኋላ ከደጋፊዎች መሀል ቁሳቁሶች የተወረወሩ ሲሆን ጨዋታውም ለጥቂት ደቂቃዎች ለመቋረጥ መገደዱ ይታወሳል።

ፌዴሬሽኑም ለጨዋታው መረበሽ ሲዳማ ቡናን ጥፋተኛ በማለት አንድ ጨዋታ በዝግ እንዲጫወት እንዲሁም 50 ሺህ ብር እንዲከፈል ተወስኖበት የነበረ ቢሆንም ክለቡ ዐምና በመጨረሻ የሊግ መርሀ ግብር ከወልዋሎ ጋር ሲጫወት በይግባኝ በክፍት ስታዲየም በመጫወቱ ምክንያት ወደዚህኛው የውድድር ዘመን ተሸጋግሯል።

በዚህም በቀጣዩ ዕሁድ በሜዳው ስሑል ሽረን ሲገጥም በዝግ ያለ ተመልካች እንዲያከናውን ሲወሰን የገንዘብ ቅጣቱንም እንዲከፍል መወሰኑን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ