የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ሳምንት ቁጥሮች – ጎሎች እና ካርዶች

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመርያ ሳምንት ባሳለፍነው እሁድ እና ሰኞ መካሄዱ ይታወሳል። በነዚህ ጨዋታዎች ላይ ተመዘገቡ ቁጥራዊ መረጃዎችን ከጎሎች እና ካርዶች አንፃር እንደሚከተለው አሰናድተነዋል።

ጎሎች

– በአንደኛው ሳምንት በተከናወኑ 8 ጨዋታዎች 13 ጎሎች ሲቆጠሩ ወልዋሎ 3 ጎሎች በማስቆጠር ከፍተኛ ነው።

– ከ8 ጨዋታዎች በአምስቱ ላይ ቢያንስ አንድ ጎል ሲቆጠር ሦስት ጨዋታዎች ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። ከ16 ክለቦች ደግሞ ሰባቱ ብቻ ጎል አስቆጥረው ሲወጡ ዘጠኙ ያለ ጎል ጨዋታቸውን አጠናቀዋል።

– ከ13 ጎሎች መካከል አስራ አንድ ጎሎች ከክፍት ጨዋታ የተቆጠሩ ሲሆን አንደኛው በፍፁም ቅጣት ምት ቀሪው ደግሞ ከፍፁም ቅጣት ምት የተመለሰ ኳስ ጎል ሆኗል።

– ከ13 ጎሎች መካከል 12 በእግር ተመትተው የተቆጠሩ ሲሆን አንድ ብቻ (ደስታ ጊቻሞ) በግምባሩ ገጭቶ አስቆጥሯል።

– ከ13 ጎሎች መካከል አስራ ሁለቱ ሳጥን ውስጥ በሚገኝ ተጫዋች የተቆጠሩ ሲሆን አንድ ጎል (ሰመረ ሐፍታይ – ሰበታ ከተማ ላይ) ብቻ ከሳጥን ውጪ የቆጠረች ሆና ተመዝግባለች።

– በግለሰብ ደረጃ 11 ተጫዋቾች በጎል አስቆጣሪዎች ሰንጠረዥ ሲካተቱ አንድ ጎል በራስ መረብ ላይ የተቆጠረ ነው። ሰመረ ሐፍታይ ሁለት ጎል ያስቆጠረ ብቸኛውም ተጫዋች ሆኗል።

ካርዶች

– በአንደኛው ሳምንት ስምንት ጨዋታዎች በአጠቃላይ 13 ቢጫ ካርዶች ተመዘዋል።

– ከቢጫ ካርዶቹ መካከል 11 ለተጫዋቾች የተመዘዙ ሲሆኑ ሁለቱ ደግሞ በአሰልጣኞች ቡድን አባላት ላይ የተመዘዙ ናቸው። የሽረው ምክትል አሰልጣኝ መብራህቱ ፍስሀ እና የመቐለው ምክትል አሰልጣኝ ጎይቶም ኃይለ የማስጠንቀቂያ ካርዱን የተመለከቱ ናቸው።

– ፋሲል ከነማ በሦስት ተጫዋቾች በርካታ ካርድ የተመዘዘበት ክለብ ሲሆን አዳማ ከተማ፣ ወላይታ ድቻ፣ ሲዳማ ቡና፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ባህር ዳር ምንም ካርድ ያላስተናገዱ ክለቦች ሆነዋል።

– በዚህ ሳምንት ሁለት ቀይ ካርዶች ተመዘዋል። የሰበታ ከተማው አዲስ ተስፋዬ እና የድሬዳዋ ከተማው ዘሪሁን አንሼቦ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ የተወገዱ ተጫዋቾች ናቸው ።


© ሶከር ኢትዮጵያ