ቅድመ ዳሰሳ | ወልዋሎ ከ ወላይታ ድቻ

በመጀመርያው ሳምንት ሙሉ ሶስት ነጥብ አግኝተው በሊጉ አናት የሚገኙት ክለቦች የሚያገናኘውን ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

በመጀመርያው ሳምንት ከሜዳቸው ውጭ ሰበታ ከተማን አሸንፈው የተመለሱት ቢጫ ለባሾቹ በነገው የሜዳቸው ጨዋታ ትልቅ ግምት ይሰጣቸዋል።

በአዲስ አበባ ዋንጫ ላይ ጥሩ የውድድር ግዜ ያላሰለፉት ወልዋሎዎች በመጀመርያው ሳምንት ወሳኝ ድል አስመዝግበው በጥሩ የአሸናፊነት መንፈስ ላይ ይገኛሉ። በቅድመ ውድድር ላይ ከተጠቀሟቸው ተጫዋቾች ብዙም ለውጥ ሳያደርጉ የአጨዋወት እና የቅርፅ ለውጥ ብቻ አድርገው የሜዳ ውጭ ጨዋታቸውን ያካሄዱት ወልዋሎዎች የነገው ጨዋታ በሜዳቸው እና በደጋፊያቸው ፊት እንደመሆኑ የማሸነፍ ጫናው የሚኖረው በእነሱ ላይ ነው። በዚህም ከመጀመርያው ሳምንት በተለየ አጨዋወት ማጥቃት ላይ መሠረት አድርገው እንደሚገቡ ይጠበቃል።

ቢጫ ለባሾቹ በነገው ጨዋታ ባልታወቀ ምክንያት ከቡድኑ ጋር ከሌለው ጁንያስ ናንጋጁቦ ውጭ በጉዳት እና በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም።

በመጀመርያው የሊጉ መርሃ ግብር የቅርብ ተቃናቃኛቸው ሲዳማ ቡናን አሸንፈው ከተጋጣሚያቸው ወልዋሎ በእኩል ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ የሚገኙት ወላይታ ድቻዎች ምንም እንኳ ጨዋታው ከሜዳቸው ውጭ ቢሆንም ቀላል ግምት አይሰጣቸውም። የጦና ንቦች የቅድመ ውድድር ጊዜያቸው ባሳለፉበት እና በመጠኑ በተላመዱት የመጫወቻ ሜዳ መጫወታቸው ለቡድኑ ጥሩ ዕድል እንደሆነ ቢታሰብም ወሳኝ አጥቂያቸው ባዬ ገዛኸኝ በጉዳት ማጣታቸው ለቡድኑ ጥሩ ዜና አይደለም።

አንዳንዴ በኳስ ቁጥጥር ብልጫ ተመስርተው ሲያስፈልግም በረጃጅም ኳሶች ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል ለመጠጋት የሚሞክሩት ወላይታ ድቻዎች በነገው ጨዋታ የመሃል ሜዳ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድ ይቸገራሉ ተብሎ ባይጠበቅም ጠጣሩ የወልዋሎ የመከላከል ክፍል ለማለፍ ግን ይቸገራሉ ተብሎ ይገመታል። በተለይም ቡድኑ ፈጣኑ አጥቂ ባዬ ገዛኸኝ እና በትግራይ ዋንጫ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ያሳየው በረከት ወልዴን በጉዳት ማጣቱ በአጨዋወቱ ላይ ለውጥ ለማድረግ ይገደዳል።

የጦና ንቦች በጉዳት ምክንያት የበረከት ወልዴ እና ባዬ ገዛኸኝ አገልግሎት የማያገኙ ሲሆን የተስፋዬ አለባቸው መሰለፍም አጠራጣሪ ነው።

የእርስ በርስ ግነኙነት

– ቡድኖቹ በሊጉ አራት ጊዜ ተገናኝተው በአስገራሚ ሁኔታ አራቱንም በአቻ ውጤት አጠናቀዋል።

– ስድስት ጎሎች በተቆጠሩበት የሁለቱ ግንኙነት ሁለቱም ቡድኖች ሦስት ሦስት ጎሎችን አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወልዋሎ (4-2-3-1)

ዓብዱልዓዚዝ ኬይታ

ገናናው ረጋሳ – ፍቃዱ ደነቀ – ዓይናለም ኃይለ – ሳሙኤል ዮሐንስ

ክብሮም ዘርዑ – አቼምፖንግ አሞስ

ሰመረ ሃፍታይ – ካርሎስ ዳምጠው – ምስጋናው ወልደዮሐንስ

ኢታሙና ኬይሙኔ

ወላይታ ድቻ (4-1-4-1)

መክብብ ደገፉ

ያሬድ ዳዊት – ደጉ ደበበ – አንተነህ ጉግሳ – እዮብ ዓለማየሁ

ተስፋዬ አለባቸው

ዘላለም ኢያሱ – ኢድሪስ ሰዒድ – ነጋሽ ታደሰ – ቸርነት ጉግሳ

ዳንኤል ዳዊት


© ሶከር ኢትዮጵያ