በፌዴሬሽኑ ስህተት ከአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ውጪ ሆኖ የነበረው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን የቶጎ ብሄራዊ ቡድን ከማጣርያው ራሱን ማግለሉን ተከትሎ ወደ ማጣርያው መመለሱ በዚህ ሳምንት መጀመርያ ይፋ መሆኑ ይታወሳል፡፡ ይህን ተከትሎም ብሄራዊ ቡድናችን በየካቲት ወር መጨረሻ አልጄርያን ይገጥማል፡፡
የብሄራዊ ቡድኑን የፊት መስመር ትመራለች ተብላ የምትጠበቀው የደደቢቷ ሎዛ አበራ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠችው አስተያየት ወደ አፍሪካ ዋንጫ ማጣርያው መመለሳቸው ደስታን እንደፈጠረላት ተናግራለች፡፡ ‹‹ ወደ ማጣርያው በመመለሳችን ደስ ብሎኛል፡፡ እድሉን ካጣን በኋላ ፌዴሬሽኑ ጥረት አድርጎ ወደ ውድድሩ መመለሳችን በግሌ በጣም አስደስቶኛል፡፡ ሃገሩን ወክሎ የመጫወት ፍላጎት እንዳለው ማንኛውም ተጫዋች በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ›› ብላለች፡፡
የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ቡድንን በአምበልነት በመምራት ለአለም ከ20 አመት በታች ዋንጫ ለማለፍ ከጫፍ ደርሳ የነበረችው ሎዛ ጥቂት ጨዋታ ባደረገችበት ዋናው ብሄራዊ ቡድንም ስኬትን ታልማለች፡፡ ‹‹ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያው አቅማችንን የምናይበት ነው፡፡ እኔም ለብሄራዊ ቡድን ከተጠራሁ ያለኝን ሁሉ ለቡድኔ ለመስጠት ተዘጋጅቻለሁ፡፡ ሃገሬንም በአፍሪካ መድረክ የተሻለ ደረጃ ለማድረስ ጥረት አደርጋለሁ፡፡ ›› ብላለች፡፡
ሎዛ በአሁኑ ሰአት በኢትዮጵያ የሴቶች እግርኳስ ዝናዋ የናኘ ተጫዋች ለመሆን በቅታለች፡፡ በአንድ ጨዋታ እቴጌ ላይ ያስቆጠረችውን 9 ግብ ጨምሮ በ5 ጨዋታ 16 ግቦች ከመረብ በማሳረፍ የሊጉን ከፍተኛ ግብ አግቢነት በመምራት ላይ ትገኛለች፡፡ በኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ቡድን ብቃቷን የተመለከቱ ተመልካቾች ግን ከምታስቆጥራቸው ግቦች ብዛት ባሻገር የሜዳ ላይ እንቅስቃሴዋ ተዳክሟል የሚል አስተያየት ይሰጣሉ፡፡
‹‹ በአቋሜ ዙርያ የተለያዩ አስተያየቶች ይኖራሉ፡፡ ለምን አስተያት ተሰጠብኝ አልልም፡፡ የተቻለኝን ሁሉ እያደረግኩና ክለቤንም በአግባቡ እያገለገልኩ እንዳለሁ ነው የሚሰማኝ፡፡ በጥሩ አቋም ላይ ለመገኘትም ጠንክሬ እየሰራሁ ነው፡፡ ማንኛውም ተጫዋች ሁልጊዜ በ100% አቋሙ ላይ መገኘት አይችልም፡፡ መውጣት እና መውረድ ይኖራል፡፡ ይህን ስል ግን ሁሉንም ነገር ጨርሳለሁ ማለቴ አይደለም፡፡ እንደተጫዋች መሻሻል እፈልጋለሁ፡፡ ሁልጊዜም የተሻለ ተጫዋች ለመሆንና ራሴን ለማሳደግ እጥራለሁ፡፡ ለዚህም ጠንክሬ እየሰራለሁ እገኛለሁ፡፡ ›› ስትል አስተያየቷን አጠቃላለች፡፡
የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ከአልጄርያ ጋር የሚያደርገው የመጀመርያ የማጣርያ ጨዋታ ከየካቲት 25-27 ባሉት ቀናት አልጀርስ ላይ የሚካሄድ ሲሆን የመልሱን ጨዋታ ከመጋቢት 9 እስከ 11 ባሉት ቀናት ውስጥ አዲስ አበባ ላይ ያደርጋል፡፡ ኢትዮጵያ ይህንን ዙር ካለፈች ከኬንያ እና ዴሞክራቲክ ኮንጎ አሸናፊ ጋር ትፋለማለች፡፡