የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሰበታ ከተማ ጨዋታ ወቅታዊ መረጃ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 2ኛ ሳምንት ዛሬ ለሚካሄደው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሰበታ ከተማ ጨዋታ በስታዲየሙ ለዝግጅት ተብሎ የተሠራው ርብራብ አለመነሳቱን ተከትሎ ያሉት ወቅታዊ መረጃዎች።

14ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች በዓል ምክንያት በካታንጋ በአጠና የተሰራው ርብራብ ከበዓሉ መጠናቀቅ በኋላ አለመነሳቱን ተከትሎ የዛሬው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የሰበታ ከተማ ጨዋታ የመካሄዱ ነገር አጠራጥሮ እንደነበረ ትናንት መዘገባችን ይታወሳል።

አሁን ባገኘነው መረጃ የተሰራው ርብራብ በዕለቱ እየጣለ ከሚገኘው ዝናብ ጋር ተደምሮ በአነስተኛ የሰው ኃይል እየፈረሰ ይገኛል። ሆኖም የማፍረስ ሥራው ዘግይቶ የጀመረ መሆኑ እስከ ጨዋታው መዳረሻ ድረስ ተጠናቆ ሜዳውን ለጨዋታ ዝግጁ ለማድረግ አዳጋች እንደሆነ ከስፍራው ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል። ምናልባትም በቀሩት ሰዓታት የሰው ኃይል በመጨመር የማፍረስ ሥራውን በፍጥነት ማጠናቀቅ ከተቻለ ጨዋታው የሚካሄድ ይሆናል።

ከደቂቃዎች በኋላ የሁለቱም ቡድኖች ተወካዮች ከዕለቱ ዳኛ እና የጨዋታ ታዛቢ ጋር በመሆን ቅድመ ስብሰባ በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚያደርጉ ሲሆን በጨዋታው መካሄድ እና አለመካሄድ ዙርያ ውይይት ይደረጋል። በቀጣይ የሚኖሩ አዳዲስ መረጃዎች ካሉም የምናደርስ ይሆናል።

*ማስታወሻ

በትላቱም ሆነ በዛሬው ዘገባችን ለመግለፅ የሞከርነው ጨዋታው በተያዘለት ሰዓት እንዳይካሄድ ለበዓሉ ማድመቂያ የተሰራው ርብራብ በአግባቡ አለመወገድ እክል ሊሆን ይችላል የሚል ነው። ሆኖም ዘገባውን ወደ ሌላ ጊዜ ተዘዋውሯል በሚል አረዳድ የተረዱ አካላት እየተመለከትን በመሆኑ በዚህ መልኩ እንዲመለከቱት እናሳስባለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ