በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ9ኛ ሳምንት 5 ጨዋታዎች ዛሬ በተለያዩ ከተሞች ተደርገዋል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአርባምንጭ ፣ ደደቢት ከጎንደር ድል ይዘው ሲመለሱ ሀዋሳ ከተማ በሜዳው ኢትዮጵያ ቡናን አሸንፏል፡፡
አርባምንጭ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስን ያስተናገደው አርባምንጭ ከተማ 1-0 ተሸንፏል፡፡ የቅዱሰ ጊዮርጊስን የድል ግብ አዳነ ግርማ በ65ኛው ደቂቃ በፍጹም ቅጣት ምት ሲያስቆጥር ፍጹም ቅጣት ምቱ የተሰጠበት መንገድ በአርባምንጭ በኩል ቅሬታን አስነስቷል፡፡ የተነሳውን ከፍተኛ ውዝግብ ተከትሎም ጨዋታው ለደቂቃዎች ለመቋረጥ ተገዶ ነበር፡፡
ከፍተኛ ውጥረት የነገሰበት እና ለግማሽ ሰአት የተቋረጠው የሀዋሳ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ በሀዋሳ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ የሃዋሳን የድል ግብ ፍርድአወቅ ሲሳይ ከእረፍት መልስ 48ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ አሳርፏል፡፡ ከግቧ መቆጠር በኋላ በሁለቱ ቡድኖች ደጋፊዎች መካከል ከፍተኛ ግርግር የተነሳ ሲሆን በግጭቱ ምክንያት ጨዋታው ለ31 ደቂቃዎች ተቋርጧል፡፡ የተነሳውን ግጭት ለማረጋጋት የልዩ ሃይል ፖሊስ እና የከተማው ከንቲባ ወደ ስታድየም መምጣትም አስፈልጓል፡፡
የሰርግ ስነስርአቱን ዛሬ እየፈፀመ የሚገኘው የሃዋሳ ከተማው የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ አምጣቸው ኃይሌ በጨዋታው እረፍት ሰአት ላይ ከሙሽሪቷ ጋር ስታድየም መገኘቱ የጨዋታው ሌላ ክስተት ሆኗል፡፡
ጎንደር ላይ ዳሽን ቢራ ደደቢትን አስተናግዶ የ1-0 ሽንፈት አስተናግዷል፡፡ የሰማያዊዎቹን የድል ግብ ከመረብ ያሳረፈው የአምናው ከፍተኛ ግብ አግቢ ሳሙኤል ሳኑሚ ነው፡፡ ናይጄርያዊው አጥቂ ከአዳነ ግርማ እና ታፈሰ ተስፋዬ ጋር በጋራ 7 ግቦች የሊጉን ከፍተኛ ግብ በጋራ 7 ግቦች የሊጉን ከፍተኛ ግብ አግቢነት እየመራ ይገኛል፡፡
ቦዲቲ ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ያስተናገደው ወላይታ ድቻ 1-1 አቻ ተለያይቷል፡፡ ከ4 ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ የመጀመርያ ነጥቡንም አሳክቷል፡፡ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኤፍሬም አሻሞ የ73ኛ ደቂቃ ግብ 1-0 ቀዳሚ ሲሆን የድቻን የአቻነት ግብ አናጋው ባደግ በ82ኛው ደቂቃ አስቆጥሯል፡፡
በሆሳዕና አቢዮ አርሳሞ ስታድየም የተደረገው የመከላከያ እና ሀዲያ ሆሳዕና ጨዋታ ካለ ግብ 0-0 ተጠናቋል፡፡ በጨዋታው ሆሳዕና ያገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ቢንያም ገመቹ መትቶ በይድነቃቸው ኪዳኔ ከሽፎበታል፡፡
አወዛጋቢ የፍፁም ቅጣት ምት ፣ ረብሻ እና ሰርግ ያስተናገደው እንዲሁም በመጀመርያ አጋማሽ ምንም ግብ ሳያስተናገድ ያለፈው የ9ኛው ሳምንት የእሁድ ውሎ ይህን በመሰለ መልኩ አልፏል፡፡ ነገ አዳማ ከተማ ወደ ሊጉ መሪነት ለመመለስ በማለም ድሬዳዋ ከተማን ድሬዳዋ ላይ ሲገጥም ወደ ደረጃ ሰንጠረዡ አናት እየተጠጋ የሚገኘው ሲዳማ ቡና ይርጋለም ላይ ኤሌክትሪክን ያስተናግዳል፡፡