ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ንግድ ባንኮች አቃቂ ላይ ግማሽ ደርዘን ጎል በማስቆጠር አሸንፈዋል

በሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ባንክ ሜዳ ላይ አቃቂ ቃሊቲን ያስተናገደው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ። ከፍፁም የበላይነት ጋር 6–1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የውድድር ዓመቱን የመጀመርያ ድሉን አሳክቷል።

ባሳለፍነው ሳምንት ንግድ ባንክ ከአዳማ ከተማ ጋር አንድ አቻ ከተለያየው ስብስቡ ግብጠባቂ ንግስት መዓዛ፣ ታሪኳ ደቢሶ፣ ሰብለ ቶጋ እና ብርቱካን ገ/ክርስቶስን በማሳረፍ በምትኩ ግብጠባቂዋ ምህረት ተሰማ፣ ብዙዓየሁ ታደሰ፣ ትዕግስት ያደታ እና ፎዚያ መሐመድን በመያዝ ወደ ሜዳ ገብተዋል። አቃቂ ቃሊቲ ከሀዋሳ ከነማ ጋር አንድ በሆነ ውጤት አቻ ከተለያየው ቡድኑ ዝናሽ መንክር ፣ ማኀሌት ታደሰ እና ፍቅረአዲስ ተስፋዬን በማሳረፍ መሠረት ገ/እግዚአብሔር፣ እየሩሳሌም ታደሰ እና ቤዛዊት ታደሰን በመያዝ ወደ ሜዳ ገብተዋል።

በፌደራል ዳኛ ምስጋና ጥላሁን በተመራው በዚህ ጨዋታ አዲስ አዳጊው አቃቂ ባሳለፍነው ሳምንት ከሀዋሳ ጋር በተጫወቱበት አጨዋወት የፊት መስመሩን በጥሩ ሁኔታ ይመሩ የነበሩቱን ሁለቱን ሰላማዊቶችን ወደ ኋላ በመመለስ እንዲከላከሉ ማድረጋቸው አቃቂ በማጥቃቱ ረገድ ድክመት እንዲኖርበት አድርጎታል። ንግድ ባንክ በአንፃሩ ኳስን ተቆጣጥሮ በመጫወትም ሆኖ ወደ ጎል በተደጋጋሚ በመድረስ እንዲሁም በልምድ የተሻሉ ተጫዋቾች የተሰባሰቡበት ቡድን እንደመሆኑ ፍፁም ብልጫ እንዲወስድ አድርጎታል። በ9ኛው ሽታዬ ሲሳይ ከመስመር አጥብባ ሳጥን ውስጥ በመግብታ ወደ ጎል የመታችው የግቡ ቋሚ የመለሰው የጎል አጋጣሚ የንግድ ባንክ የመጀመርያው ሙከራ ነበር።

መሐል ሜዳ ላይ ተገድቦ በሚደረግ እንቅስቃሴ በቀጠለው ጨዋታ በ27ኛው ደቂቃ ረሒማ ዘርጋው ከመሐል ሜዳ የተሻገረላትን ኳስ በመያዝ ወደ ፊት በመሔድ ከግብጠባቂዋ ሺብሬ ካንኮ ጋር ተገናኝታ ግብጠባቂዋ ያደነችባትን ኳስ ለንግድ ባንክ ጎል መሆን የሚችል ሳይጠቀሙበት የቀረ ሌላ የጎል አጋጣሚ ነበር። አቃቂዎች ጥሩ ኳስ ለመጫወት እንቅስቃሴ ቢያደርጉም ሦስተኛው የሜዳ ክፍል በመግባት የግብ ዕድል ለመፍጠር ቢነሞክሩም ከልምድ ችግር ጋር በተያያዘ በቀላሉ በንግድ ባንክ ተከላካዮች በተደጋጋሚ ኳስ ይነጠቁ ነበር።

ጎል ለማስቆጠር ይዘግዩ እንጂ በእንቅስቃሴ የተሻሉ የነበሩት ንግድ ባንኮች ጥረታቸው ተሳክቶ የመጀመርያ ጎላቸውን ማስቆጠር ችለዋል። በ29ኛው ደቂቃ ከቆመ ኳስ ህይወት ደንጊሶ ወደ ጎል ያሻገረችውን ፎዚያ መሐመድ ኳሱ ጋር ደርሳ ወደ ጎል የመታችውን ግብጠባቂዋ ሽብሬ ለማዳን ሞክራ ስትተፋው ነፃ አቋቋም ላይ የነበረችው ረሒማ ዘርጋው ተረጋግታ ወደ ጎልነት በመቀየር ንግድ ባንክን ቀዳሚ ማድረግ ችላለች። በተለይ ከ35ኛው ደቂቃ በኃላ ወደ ጎል መድረስ የቻሉት አቃቂዎች ከብስለት ችግር ያገኙትን አጋጣሚ ሳይጠቀሙ ቀሩ እንጂ ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን የጎል ዕድሎችን አግኝተው ነበር። የመጀመርያው አጋማሽም በንግድ ባንክ 1-0 መሪነት ተጠናቆ ወደ እረፍት አምርተዋል።

ፍፁም የበላይነትን በሁለተኛው አጋማሽ የወሰዱት ንግድ ባንኮች በ47ኛው ደቂቃ ከመስመር የተሻገረውን የአቃቂ ቃሊቲ ተከላካዮች ኳሱን አግኝተው ባግባቡ ከግብ ክልላቸው ባለማራቃቸው ምክንያት ያገኘችውን ኳስ ሽታዬ ሲሳይ ሁለተኛ ጎል አስቆጥራለች። ከሁለት ደቂቃ በኃላ ደግሞ ከማዕዘን ምት ተደርቦ የተመለሰውን ገነሜ ወርቁ አግኝታ ሦስተኛ ጎል በማስቆጠር የጎል መጠኑን ከፍ አድርጋለች።

በመሐል ሜዳ ላይ የአዲስ ፈራሚዋ እመቤት አዲሱን መልካም የሚባል አገልግሎት እያገኙ ያሉት ንግድ ባንኮች እመቤት አዲሱ ከሳጥኑ ጠርዝ አመቻችታ ለትግስታ ያደታ የተጠቻትን ወደ ጎል በቀጥታ በጥሩ ሁኔታ ብትመታውም በአቃቂ በኩል ጥሩ ኳሶችን ማዳን የቻለችው ግብጠባቂዋ ሽብሬ ወደ ውጭ ያወጣቸው አራተኛ ጎል መሆን የሚችል ዕድል ነበር።

አቃቂዎች የንግድ ባንክን የማጥቃት ኃይል መቆጣጠር አቅቷቸው የታዩ ሲሆን 60ኛው ደቂቃ ላይ ሽታዬ ሲሳይ ከተከላካዮች መሐል የተጣለላትን ኳስ ወደ ጎልነት በመቀየር የንግድ ባንክን የጎል መጠን ወደ አራት አድርሳዋለች። ብዙም ሳይቆይ ራሷ ሽታዬ ሐትሪክ መሰራት የምትችልበትን እድል በሁለት አጋጣሚ በ62ኛ እና 72ኛው ደቂቃ አግኝታ በማይታመን መልኩ ሳትጠቀም ቀርታለች።

በመሐል ሜዳ ላይ የንግድ ባንክ ተጫዋቾች የተፈጠረውን ስህተት በመጠቀም ተቀይራ የገባችው መሐሪ በቀለ 77ኛው ለአቃቂ ቃሊቲ ማስተዛዘኛ ብቸኛ አንድ ጎል አስቆጥራለች።

በጨዋታው የአቋቋም መስመር በመስራት ረገድ ክፍተት የታየባቸው አቃቂዎች በ80ኛው ደቂቃ በረሒማ ዘርጋው አማካኝት አምስተኛ ጎል ለማስተናገድ ተገደዋል። ካገባችው በላይ ያመከነቻቸው ዕድሎች ቢኖሩም በመጨረሻም ለቡድኗ ስድስተኛ ለራሷ ደግሞ ሐትሪክ የሰራችበትን ጎል ሽታዬ ሲሳይ ከቅጣት ምት ግሩም ጎል አስቆጥራለች። ሽትታዬም የውድድር ዓመቱ ሁለተኛ ሐት-ትሪክ የሰራች ተጫዋች ስትሆን የውድድሩም ኮከብ ጎል አስቆጣሪነትም በአራት ጎሎች እየመራች ትገኛለች።

ጨዋታው በንግድ ባንክ ፍፁም የበላይነት 6–1 በሆነ ውጤት አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የውድድር ዓመቱን የመጀመርያ ሦስት ነጥብ አሳክቷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ