​ሴካፋ 2017፡ ኢትዮጵያ በመጀመርያ የምድብ ጨዋታዋ ደቡብ ሱዳንን አሸንፋለች

በሴካፋ ሲኒየር ቻሌንጅ ዋንጫ የመጀመሪያ ጨዋታውን ከደቡብ ሱዳን ጋር በካካሜጋ ቡኩንጉ ስታዲየም ያደረገው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን 3-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ምድቡን መምራት ችሏል፡፡ ዋሊያዎቹ በጨዋታው በደቡብ ሱዳን እምብዛም ሳይፈተኑ ማሸነፍ ችለዋል፡፡

ዋልያዎቹ በ4-1-2-3 ቅርፅ ወደ ሜዳ የገቡት ሲሆን አዲስ ግደይ ከተፈጥሯዊ የመስመር አጥቂነት ሚናው በተቃራኒ የቀኝ መስመር ተከላካይ ሆኖ ጨዋታውን ሲጀምር በሁለተኛው አጋማሽ ቦታውን ለሄኖክ አዱኛ አስረክቦ ከሜዳ ወጥቷል፡፡

ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል በመድረስም ይሁን ኳስ በመቆጣጠር ኢትዮጵያዎች ተሽለው ሲታዩ ደቡብ ሱዳን በለግላጋ ቁመታቸው የአየር ላይ ኳስ የበላይ መሆናቸውን የተረዱት የኢትዮጵያ ተጫዋቾች ኳስ በአጭር ቅብብል ለመጫወት መምረጣቸው በቀላሉ የጠሩ የግብ እድሎችን ለመፍጠር አስችሏቸዋል፡፡ በተለይ በመጀሪያዎቹ 11 ደቂቃዎች ያለቀላቸውን ሶስት የግብ እድሎችን ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል፡፡ በአምስተኛው ደቂቃ ዳዋ ሆጤሳ ከ17 ሜትር አክርሮ መሬት ለመሬት የሞከረውን ኳስ የደቡብ ሱዳኑ ጁማ ጄናሬ ሲመልስበት በቅርበ ርቀት ላይ የተገኘው አቡበከር ሳኒ በማይታመን መልኩ ኳሷን ወደ ውጪ ልኳታል፡፡ ከሁለት ደቂቃዎች በኃላ ከመስመር በጥሩ ቅብብል ተመስርቶ የመጣውን ኳስ አቡበከር አግኝቶ ቢሞክርም ጁማ ኳሷን አውጥቷታል፡፡ በ11ኛው ደቂቃ አሁንም አቤል ያለው እና አብዱራህማን ሙባረክ በአንድ ሁለት ወደ ሳጥን ውስጥ ገብተው አቤል ለዳዋ ቢያቀብለውም ነፃ የነበረው የአዳማው አጥቂ በግቡ አናት ኳሷን ሰዷታል፡፡

ዋልያዎቹ በፈጣን ቅብብል ረዘም ያለ ደቂቃ በደቡብ ሱዳን የግብ ክልል በመድረስ ሙከራዎችን ለማድረግ ጥረት አድርገው በ24ኛው ደቂቃ ሳምሶን ጥላሁን አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ አቤል ያለው ተጠቅሞ ኢትዮጵያን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል፡፡ በኢትዮጵያ መለያ የመጀመሪያውን ጨዋታ ያደረገውን አቤል ግሩም እንቅስቃሴ በማድረግ በጨዋታው ላይ ነጥሮ መውጣት ችሏል፡፡ ከአራት ደቂቃዎች በኃላም በአጫጭር ቅብብሎች ወደ ደቡብ ሱዳን የግብ ክልል የደረሱት ዋሊያዎቹ በአቤል አማኝነት ጥሩ እድል ቢያገኙም አጥቂው እድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡

ደቡብ ሱዳኖች ወደ ጨዋታው ለመመለስ በማሰብ ሁለት ተጫዋቾችን በደቂቃ ልዩነት ቀይሮ በማስገባት የታክቲክ ለውጥ ቢያደርጉም በጨዋታው ላይ ተፅእኖ መፍጠር ተስኗቸው ታይተዋል፡፡ በ41ኛው እና 45ኛው ደቂቃ አብዱራህማን ግብ ማስቆጠር የሚችልባቸው ሁለት እድሎችን አግኝቶ ሳይጠቀምባቸው ቀርቷል፡፡ በተለይ በ45ኛው ደቂቃ  አቤል የደቡብ ሱዳንን ተከላካይ ኳስ በማስጣል ለአብዱራህማን ግብ የማስቆጠር በቂ የሆነ ግዜ እና ቦታ ቢሰጠውም የፋሲል ከነማው አጥቂ ኳስ በግቡ አናት ሰዷታል፡፡

ከእረፍት መልስ የዋሊያዎቹ የጨዋታ ብልጫ የቀጠለ ሲሆን የኳስ ቁጥጥሩ ግን ሁለት ተጨማሪ ግቦች  ከተቆጠሩ በኃላ እየቀነሰ መጥቷል፡፡ በ50ኛው ደቂቃ አበባው ቡታቆ በረጅሙ የጣለውን ኳስ አቤል እራሱን ነፃ በማድረግ ከግብ ክልሉ እየወጣ በነበረው ጁማ አናት ላይ ኳሷን በመላክ የኢትዮጵያን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል፡፡ ከሰባት ደቂቃዎች በኃላ ደግሞ የደቡብ ሱዳን ተከላካዮች መዘናጋትን ተከትሎ አቡበከር ሳኒ ሶስተኛው ግብ ጁማን በማቆም አስቆጥሯል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሶስተኛውን ግብ ካስቆጠሩ በኃላ ደቡብ ሱዳኖች ለመጫን መሞከራቸውን ተክትሎ ኳስን በማስጣል እና በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ሲሞክሩ ተስተውሏል፡፡ ሆኖም ስኬታማ ያልነበረው የማጥቃት ሽግግር በቀላሉ ዋልያዎቹ ተጨማሪ ግቦችን እንዳያስቆጥሩ ሲያግዳቸው ተስተውሏል፡፡ በ81ኛው ደቂቃ አቤል ሐት-ትሪክ የሚሰራበትን እድል ጁማ በድንቅ ሁኔታ ሲመልስ በ85ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ጆሴፍ ሴሊስቲኖ ሄኖክ አዱኛን በእንቅስቃሴ በማለፍ ወደ ግብ የሞከረው ኳስ ቋሚውን መልሶበታል፡፡ ከደቂቃ በኃላ ዶሚኒክ ፕሪቲኖ ያገኘውን ያለቀለት ኳስ ቀጥታ ወደ ታሪክ ጌትነት በመምታት አምክኗል፡፡ ዋሊያዎቹ በቀሪዎቹ ደቂቃዎች መሪነታቸውን በማስጠበቅ ሙሉ ሶስት ነጥብ ማሳካት ሲችሉ በደቡብ ሱዳን ላይ ያላቸውን የማሸነፍ ሪከርድም ወደ ሶስት ከፍ አድርገዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በቀጣይ ጨዋታው ሐሙስ ቡሩንዲን በ9፡00 ሰዓት ሲገጥም ደቡብ ሱዳን ከዩጋንዳ አርብ ይገናኛሉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *