የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 5ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅዳሜ እና እሁድ በተለያዩ ከተሞች ተካሂደዋል፡፡ በምድብ ሀ መሪው ወልድያ የመጀመርያ ሽንፈቱን ሲያስተናግድ አዲስ አበባ ፖሊስ ወደ ምድቡ መሪነት ተመልሷል፡፡
መቐለ ከተማ እና ወሎ ኮምቦልቻ ያለመሸነፍ ጉዟቸውን አስጠብቀዋል
ሱሉልታ ከተማ በሜዳው ጨዋታ የሚያደርግበት ሁኔታ ላይ የማይገኝ በመሆኑ የሜዳውን ጨዋታዎች አዲስ አበባ ስታድየም እና መድን ሜዳ ላይ ለማድረግ ተገዷል፡፡ ሱሉልታ ትላንት 5፡00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም መቐለ ከተማን አስተናግዶ 2-0 በሆነ ውጤት ተሸንፏል፡፡ የመቐለን የድል ግብ ከመረብ ያሳረፉት ቢንያም ጌታቸው እና ሃብታሙ ነጋሽ ናቸው፡፡ መቐለ ከሱሉልታ ባገኘው 3 ነጥብ ታግዞ በ11 ነጥቦች 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
ሌላው በሜዳው ጨዋታ ማድረግ ያልቻለው ሰበታ ከተማ ወሎ ኮምቦልቻን ለመግጠም የመድን ሜዳን ለመጠቀም ተገዷል፡፡ በጨዋታው ሰበታ ከተማ ኤርሚያስ ፍስሃ ባስቆጠረው ግብ ቀዳሚ ሲሆን እድሪስ ሰኢድ የወሎ ኮምቦልቻን የአቻነት ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡ ውጤቱን ተከትሎ ከምድብ ሀ መቐለ ከተማ እና ወሎ ኮምቦልቻ በውድድር ዘመኑ ሽንፈት ያላስተናገዱ ክለቦች ሆነዋል፡፡
ወልድያ በከባድ ሽንፈት የ100% ግስጋሴው ተገትቷል
የምድብ ሀ መሪ ወልድያ ወደ ባህርዳር አቅንቶ በአማራ ውሃ ስራ ከፍተኛ ሽንፈት አስመዝግቧል፡፡ በአማራ ውሃ ስራ 4-0 አሸናፊነት በተጠናቀቀው ጨዋታ ግቦቹን በቀለ ገነነ ሁለት ፣ ፍጹም ከበደ እና ፍቅረሚካኤል አለሙ አንድ አንድ ከመረብ አሳርፈዋል፡፡ ይህ ውጤት ለወልድያ የመጀመርያ ሽንፈት ሲሆን ጥሩ አጀማመር ላላደረገው አማራ ውሃ ስራ ደግሞ የውድድር ዘመኑ የመጀመርያ ድል ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
መድን በሜዳው ማሸነፍ ከብዶታል
ኢትዮጵያ መድን አሁንም በሜዳው ያደረገውን ጨዋታ ማሸነፍ አልቻለም፡፡ ባህርዳር ከተማን ያስተናገደው የአሰልጣኝ ወርቁ ደርገባ ቡድን 2-2 አቻ ተለያይቷል፡፡ ሀብታሙ ወልዴ ሁለቱንም የመድን ግቦች ሲያስቆጥር የባህርዳር ከተማን ግቦች ተዘራ ጌታቸው እና ውብሸት ካሳዬ ከመረብ አሳርፈዋል፡፡ የአቻ ውጤቱ ሁለቱንም ቡድኖች በደረጃ ሰንጠረዡ ከወገብ በታች እንዲቀመጡ አስገድዷቸዋል፡፡
ፋሲል ከተማ እና አአ ፖሊስ ወደ አሸናፊነት ተመልሰዋል
ጎንደር ላይ ሙገር ሲሚንቶን ያስተናገደው ፋሲል ከተማ 2-0 በማሸነፍ ወደ አሸናፊነት ተመልሷል፡፡ የአፄዎቹን የድል ግቦች በክረምቱ በአዳማ ከተማ የጥቂት ወራት ቆይታ አድርጎ ፋሲልን የተቀላቀለው ተሾመ ሆሼ እና የቀድሞው የደደቢት አማካይ ከድር ኸይረዲን ከመረብ አሳርፈዋል፡፡
ሌላው ካለፈው ሳምንት ሽንፈት ያገገመው ክለብ አአ ፖሊስ ነው፡፡ ቅዳሜ በአበበ ቢቂላ ስታድየም ኢትዮጵያ ውሃ ስራን የገጠመው አአ ፖሊስ 1-0 አሸንፏል፡፡ ዘንድሮው የአአ ፖሊስ ጥሩ አጀማመር ዋንኛው ተጠቃሽ አባይነህ ፌኖ ብቸኛዋን የድል ግብ አስቆጥሯል፡፡
ደብረብርሃን እና አክሱም ግርጌውን መላቀቅ አልቻሉም
በትግራይ ደርቢ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከአክሱም ከተማ 1-1 አቻ ተለያይተዋል፡፡ ወልዋሎን ግብ ካሜሩናዊው ቢኩላ ኢማኑኤል ከመረብ ሲያሳርፍ ያሬድ ከበደ ለአክሱም ከተማ አስቆጥሯል፡፡ የአቻ ውጤቱ አክሱምን በ2 ነጥብ 15ኛ ደረጃ እንዲቀመጥ ሲያደርገው ወልዋሎን ወደ 8ኛ ደረጃ አውርዶታል፡፡
ቡራዩ ላይ ቡራዩ ከተማ ከሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን ነጥብ ተጋርቷል፡፡ ቡራዩ አሸናፊ ባስቆጠረው ግብ የመጀመርያውን አጋማሽ በ 1-0 መሪነት ሲያጠናቅቅ በሁለተኛው አጋማሽ ብሩክ አቡዲ ደብረብርሃንን አቻ ያደረገች ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡ ይህ ውጤት የደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲን መፍረስ ተከትሎ ወደ ከፍተኛ ሊግ ላደገው ደብረብርሃን በውድድር ዘመኑ የመጀመርያ ነጥብ አስገኝቷል፡፡ ደብረብርሃን የደረጃ ሰንጠረዡን ግርጌ በ1 ነጥብ ይዟል፡፡
የምድብ ሀ የደረጃ ሰንጠረዥ ይህንን ይመስላል:-