የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ በ5ኛ ሳምንት. . .

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 5ኛ ሳምንት ቅዳሜ እና እሁድ በተለያዩ ከተሞች ተደርጓል፡፡ አአ ከተማ የመጀመርያ ሽንፈቱን ሲያስተናገድ ጅማ አባቡና መሪውን ተጠግቷል፡፡

ጅማ አባ ቡና በድንቅ ደጋፊዎቹ ታግዞ የአአ ከተማን 100% የአሸናፊነት ገትቷል

ጅማ ላይ አዲስ አበባ ከተማን ያስተናገደው ጅማ አባ ቡና 3-1 በማሸነፍ የአዲስ አበባ ከተማን የድል ጉዞ ገትቷል፡፡ በመካከላቸው ያለውን የነጥብ ልዩነትም ወደ 1 ነጥብ ማጥበብ ችሏል፡፡ ጅማ አባቡናዎች በአስደናቂ የደጋፊ ድባብ ታግዘው በፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ሶስቱንም ግቦች ለማስቆጠር ከግማሽ ሰአት ያነሰ ጊዜ ብቻ አስፈልጓቸዋል፡፡ የውሃ ሰማያዊ ለባሾቹን ግቦች ኦሜ መሃመድ 2 እንዲሁም ፓትሪክ ኑቡምባ አንድ አስቆጥረዋል፡፡ ቀስ በቀስ ጨዋታውን የተቆጣጠሩት አዲስ አበባ ከተማዎች ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩ ተቀይሮ በገባው ፍፁም ካርታ አማካኝነት ግብ አስቆጥረዋል፡፡ ሽንፈቱ አዲስ አበባ ከተማን ከመሪነቱ ባያወርደውም ከተከታዩ ጅማ አባቡና ጋር ያለው የነጥብ ልዩነት ወደ 1 ጠቧል፡፡

ሻሸመኔ ከተማ መሪ የመሆን እድሉን ሳይጠቀም ሲቀር ሀላባ ወደ መሪዎቹ ተጠግቷል

ወደ ባቱ የተጓዘው ሻሸመኔ ከተማ ከባቱ ከተማ ጋር ያለ ግብ አቻ ተለያይቷል፡፡ የአቻ ውጤቱ ሻሸመኔን በ10 ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ ሲያስቀምጠው ባቱ ከተማ በ5 ነጥቦች ከወራጅ ቀጠናው በቅርብ ርቀት እንዲቀመጥ አድርጎታል፡፡

ሀላባ ከተማ በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎችን በማሸነፍ ከመሪው አዲስ አበባ ያለውን ርቀት ወደ 2 አጥብቧል፡፡ በሜዳው ደቡብ ፖሊስን የገጠመው ሀላባ 2-1 አሸንፏል፡፡ የሀላባን የድል ግቦች ሰኢድ ግርማ እና አቦነህ ገነቱ ከመረብ ሲያሳርፍ ወንድሜነህ አይናለም የደቡብ ፖሊስን ግብ አስቆጥሯል፡፡

DDP

ሳምንቱ ለድሬዳዋ አስደሳች ሆኗል

በከፍተኛ ሊጉ የሚካፈሉት ሁለቱ የድሬዳዋ ክለቦች ድል ቀንቷቸዋል፡፡ አበበ ቢቂላ ላይ አአ ዩኒቨርሲቲን የገጠመው ድሬዳዋ ፖሊስ 1-0 አሸንፏል፡፡ መድንን ለቆ የትውልድ ከተማውን ክለብ ዘንድሮ የተቀላቀለው ዮርዳኖስ አባይ የፖሊስን ወሳኝ የድል ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡  ሌላው የድሬዳዋ ክለብ ናሽናል ሴሜንት ጅንካን ድሬዳዋ ላይ ናሽናል ሴሜንት ጅንካ ከተማን 3-0 አሸንፏል፡፡ የናሽናል ሴሜንትን የድል ግቦች ያስቆጠሩት የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና አማካይ መሃመድ ጀማል (2) እና አብነት መንግስቱ ናቸው፡፡

ዛሬ በተደረገ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ አዳማ ከተማን 2-0 ማሸነፉን ተከትሎ ሶስቱም የድሬዳዋ ክለቦች ውጤታማ ሳምንት ማሳለፍ ችለዋል፡፡

ጅማ ከተማ መንሸራተቱን ቀጥሏል

ወደ ነገሌ ያመራው ጅማ ከተማ በነገሌ ቦረና 2-0 ተሸንፏል፡፡ የነገሌ ቦረናን ሁለቱንም የድል ግቦች ከመረብ ያሳረፈው ዳግም በቀለ ነው፡፡ ዳግም ወሳኝ ግቦችን በማስቆጠር ለነገሌ የዘንድሮ ጉዞ ተጠቃሽ ተጫዋች ሆኗል፡፡

ሽንፈቱ ለክፍሌ ቦልተናው ጅማ ከተማ 2ኛ ተከታታይ ሽንፈት ሲሆን ካለፉት 3 ጨዋታዎች ማግነት ከሚገባው 9 ነጥብ 1 ብቻ አሳክቶ ወደ 6ኛ ደረጃ አሽቆልቁሏል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ መጥፎ አጀማመር አስገራሚ ሆኗል

በአበበ ቢቂላ ስታድየም ነቀምት ከተማን ያስተናገደው ፌዴራል ፖሊስ 2-1 ተሸንፏል፡፡ የነቀምት ከተማን የድል ግብ መስፍን መገርሳ እና ማንያዘዋል ጉዳዩ ሲያስቆጥሩ ይትባረክ በዙ የፌዴራል ፖሊስን ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡ ፌዴራል ፖሊስ እስካሁን ምንም ጨዋታ ያላሸነፈ ሲሆን 2 ነጥብ ብቻ ሰብስቦ የደረጃ ሰንጠረዡን ግርጌ ከሌላው የፖሊስ ክለብ ደቡብ ፖሊስ ጋር ተጋርቷል፡፡

አርሲ ነገሌ ከወራጅ ቀጠናው የወጣበትን ድል አስመዝግቧል

አርሲ ነገሌ ላይ ወራቤ ከተማን ያስተናገደው አርሲ ነገሌ ወራቤ ከተማን 1-0 አሸንፏል፡፡ የአርሲ ነገሌን የድል ግብ ከመረብ ያሳረፈው አገኘሁ ልኬሳ ነው፡፡ ድሉ አርሲ ነገሌን ከሊጉ ግርጌ በ3 ነጥብ እንዲርቅ ሲያደርገው ተሸናፊው ወራቤ ከተማ በ7 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡

የምድብ ለ የደረጃ ሰንጠረዥ የሚከተለውን ይመስላል፡-

B

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *