የአሰልጣኞች አስተያየት | ቅዱስ ጊዮርጊስ 0-0 ስሑል ሽረ

ያለ ግብ ከተጠናቀቀው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ስሑል ሽረ ጨዋታ ፍፃሜ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።

“በዛሬው ጨዋታ እድለኞች አልነበርንም” ሰርዳን ዝቪጅሆቭ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)

ስለ ጨዋታው

“በዛሬው ጨዋታ እድለኞች አልነበርንም ፤ ጥሩ ተጫውተን ብዙ እድሎችን ብንፈጥርም የፍፁም ቅጣት ምቱን አጋጣሚ ጨምሮ መጠቀም አልቻልንም። ፍፁም ቅጣት ምቱን አስቆጥረን ቢሆን ኖሮ አራትና ከዛ በላይ ግቦችን ማስቆጠር እንችል ነበር፤ ይህ እግርኳስ ነው አንዳንድ ጊዜ እነዚህ አይነት ነገሮች ያጋጥማሉ። ስለዚህ እኛ ከዚህ ጨዋታ መንፈስ ወጥተን በቀጣይ ከጅማ ጋር ስለምናደርገው ጨዋታ ማሰብ ይኖርብናል።”

ስለ ሽረ አቀራረብ

“እነሱ ወደዚህ የመጡት አንድ ነጥብ ይዘው ለመሄድ ነው፤ ሙሉ ጨዋታውን በመከላከል የሚፈልጉትን ነገር አሳክተዋል። ይህም የእግርኳስ አንዱ መንገድ ነው።”

“ያቀድነውን ስኬታማ በሆነ መልኩ መተግበር ችለናል” ሳምሶን አየለ (ስሑል ሽረ)

ስለ ጨዋታው

“ከሁለት ተከታታይ ሽንፈት በኋላ ያደረግነው ጨዋታ ከመሆኑና የዛሬው ተጋጣሚያችን የበርካታ ደጋፊዎች ባለቤት ከሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያደረግነው ጨዋታ እንደመሆኑ ያስፈልገን የነበረውን ወሳኝ አንድ ነጥብ አግኝተናል። መከላከል ላይ ትኩረት በማድረግ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ሞክረናል። በዚህም በሁለቱም አጋማሾች ያቀድነውን ስኬታማ በሆነ መልኩ መተግበር ችለናል። ካሉብን ተደራራቢ ችግሮች አንፃር የዛሬው ውጤት ለቀጣይ መነሳሻ ይሆነናል።

ስለ ዳኝነቱ

“የእግርኳስ ሕግ ዓለም አቀፍ ነው። እኛም ሀገር ዳኞቻችን በሕግ እውቀት ረገድ ችግሮች የሉም፤ ነገርግን አተገባበር ላይ ክፍተቶች አሉ። አሁን እንዲህ ነው ብዬ አስተያየት መስጠት ባልችልም እኛ ላይ የተሰጠው ፍፁም ቅጣት ምት አግባብ አይደለም፤ በዚህ ቅር ተሰኝቻለው። በዚህ ሁኔታ ሕጉ በአግባቡ እየተተገበረ ነው ለማለት ይከብደኛል።”


© ሶከር ኢትዮጵያ