53 ክለቦች በ7 ምድቦች ተከፍለው የሚወዳደሩበት የ2008 የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሊግ ባለፈው ቅዳሜ ተጀምሯል፡፡ የመክፈቻ ጨዋታዎችም ቦዲቲ እና ጋርዱላ ላይ ቅዳሜ እለት ተደርገዋል፡፡
8 ክለቦች በሚሳተፉበት የምስራቅ ዞን ቢሾፍቱ ከተማ ጃሊ ጅግጅጋን አስተናግዶ 0-0 በሆነ አቻ ውጤት ሲለያይ ወደ ሐረር የተጓዘው ሞጆ ከተማ ሐረር ሲቲን 2-1 በማሸነፍ ድንቅ የውድድር ዘመን አጀማመር አድርጓል፡፡ የቀድሞው የፕሪሚየር ሊግ ክለብ መተሃራ ስኳር ወደ ጅግጅጋ ተጉዞ ከሶማሌ ፖሊስ 1-1 በመለያየት አንድ ነጥብ ይዞ ተመልሷል፡፡ በ1990ዎቹ አጋማሽ የፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ የነበረው ወንጂ ስኳር የድሬዳዋው አሊ ሐብቴ ጋራዥን አስተናግዶ 2-1 በሆነ ውጤት አሸንፏል፡፡
በማዕከላዊ ዞን ምድብ ሀ 9 ክለቦች የሚሳተፉ ሲሆን ልደታ የዚህ ሳምንት አራፊ ቡድን ሆኗል፡፡ ቡታጅራ ላይ ቡታጅራ ከተማ ከለገጣፎ ፣ ዱከም ላይ ዱከም ከተማ ከቦሌ በተመሳሳይ ካለ ግብ አቻ ሲለያዩ አበበ ቢቂላ ላይ ንፋስ ስልክ ከ የካ 1-1 አቻ ተለያተዋል፡፡ መቂ ላይ ቱሉ ቦሎን ያስተናገደው መቂ ከተማ 2-1 አሸንፏል፡፡
በሰሜን ዞን ምድብ ሀ 7 ክለቦች ሲሳተፉ የዚህ ሳምንት አራፊ ቡድን ደባርቅ ሆኗል፡፡ አምባ ጊዮርጊስ በሜዳው በዳሞት ከተማ 1-0 ሲሸነፍ ደብረማርቆስ አማራ ፖሊስን ዳባት ከተማ አዊ እምፒልታቅን በተመሳሳይ 2-0 ውጤት አሸንፈዋል፡፡
6 ክለቦች በሚሳተፉበት የሰሜን ዞን ምድብ ለ ሽሬ እንዳስላሴ ሶሎዳ አድዋን 2-1 ሲረታ ወደ መቐለ የተጓዘው ደሴ ከተማ ዋልታ ፖሊስን 3-2 አሸንፎ ተመልሷል፡፡ ላሊበላ ላይ ላስተ ላሊበላ ትግራይ ውሃ ስራን 3-1 አሸንፏል፡፡
በደቡብ ዞን ምድብ ለ 9 ክለቦች ሲሳተፉ ባሌ ሮቤ የዚህ ሳምንት አራፊ ቡድን ሆኗል፡፡ ዲላ ላይ ዲላ ከተማ አንበሪቾን 2-1 ሲያሸንፍ ቦዲቲ ላይ ወላይታ ሶዶ ጎፉ ባሪንቼን ፣ ኮንሶ ላይ ኮንሶ ኒውዮርክ ጎባ ከተማን በተመሳሳይ 1-0 ውጤት አሸንፏል፡፡ ጋርዱላ ላይ ቡሌ ሆራን ያስተናገደው ጋርዱላ 2-0 ተሸንፏል፡፡
በማዕከላዊ ዞን ምድብ ለ 8 ክለቦች የሚሳተፉ ሲሆን ሆለታ ላይ ሆለታ ከተማ አምቦ ከተማን 2-0 ፣ ወሊሶ ላይ ወሊሶ ከተማ ጨፌ ዶንሳን 3-0 ድል አድርገዋል፡፡ ዛሬ አበበ ቢቂላ ላይ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች አራዳ ቦሌ ገርጂ ዩኒየንን 1-0 ሲያሸንፍ የአበበ ቢቂላ ስታድየም የሚገኝበት ክፍለከተማ ክለብ የሆነው አዲስ ከተማ ወልቂጤን አስተናግዶ 1-1 አቻ ተለያይቷል፡፡
6 ክለቦች በሚሳተፉበት የደቡብ ዞን ምድብ ሀ ሊደረጉ የነበሩ ጨዋታዎች ለሌላ ጊዜ ተላልፈዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሊግ በ7 ዞኖች ከተካሄደ በኋላ ከየዞኑ 1ኛ እና 2ኛ የሚወጡ 14 ክለቦች እንዲሁም ጥሩ 3ኛ የሆኑ 2 ቡድኖች በአጠቃላይ 16 ክለቦች በተመረጠ ከተማ የማጠቃለያ ውድድር አድርገው የግማሽ ፍጻሜ የሚደርሱ ክለቦች እንዲሁም በሩብ ፍጻሜው የሚወድቁ 4 ክለቦች ደግሞ እርስ በእርስ ጨዋታ አድርገው ሁለት አሸናፊ ክለቦች በአጠቃላይ 6 ክለቦች ለ2009 የኢትዮጵያ ከፍተና ሊግ አላፊ ይሆናሉ፡፡
ፎቶ ፡ ከላይ ወልቂጤ ከተማ ፤ ከታች አራዳ