የብሄራዊ ስታዲየም ግንባታን አስመልክቶ ገለፃ ተደረገ

ገርጂ አካባቢ እየተገነባ የሚገኘው ብሄራዊ ስታዲየምን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት ኮሚሽን ለብዙሃን መገናኛ አባላት የመስክ ጉብኝት እና መግለጫ አከናውኗል።

ከመግለጫው በፊት በተከናወነ የመስክ ጉብኝት ስነ ስርዓት ግምባታው በምን መልኩ እየተከናወነ እንደሆነ ማብራሪያ ተሰቷል። ግምባታውን በኮንትራት ወስዶ የሚያከናውነው አማካሪ ድርጅትን (ሜም ኤች ኢንጂነሪንግ) ወክለው አቶ መለስ ለማ በሰጡት ሰፊ ማብራሪያ የተለያዩ ነጥቦችን አንስተው ለጋዜጠኞች ገለፃ አድርገዋል። እንደ አቶ መለስ ገለፃ ከሆነ 48.8 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ስታዲየሙ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ 62ሺ ተመልካች የመያዝ አቅም እንዳለው አውስተዋል። ግለሰቡ በገለፃቸው የመጀመሪያ ዙር የግምባታ ሂደቱ 99 በመቶ እንደተጠናቀቀ እና በቀጣይ የሁለተኛ ዙር የግምባታ ሂደት ብቻ ስታዲየሙን ለማገባደድ እንደቀረ ተነግረዋል። የሁለተኛ ዙር ግምባታውንም ለማከናወን የተለያዩ ተቋማት በጨረታ ተወዳድረው ተለይተው እንደታወቁ እና ኮንትራት መያዝ ብቻ እንደቀረም አቶ መለሰ አስረድተዋል።

ውብ ገፅታ ያለው ስታዲየሙ 62ሺ ተመልካች(በወንበር) ከመያዙ በተጨማሪ 3 የጋዜጣዊ መግለጫ ክፍሎች(ሳውን ፕሩፍ የሆነ)፣ 8 ቪ አይ ፒ ክፍሎች፣ 2 ቪ ቪ አይ ፒ ክፍሎች፣ ከ1000 በላይ መፀዳጃ ቤቶች(የወንድም የሴትንም ጨምሮ)፣ 10 የሚዲያ ክፍሎች፣ ከ15 በላይ ሬስቶራንቶች( በአንድ ጊዜ ከ2500 ሰው በላይ ማስተናገድ የሚችሉ) እና 7 ሊፍቶች እንዳሉት ተነግሯል። ከዋናው ስታዲየም ውጪም መለስተኛ ስታዲየሞች፣ ከ3500 በላይ የመኪና ማቆሚያ ቦታ፣ የተለያዩ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እና መዝናኛ ቦታዎች እንደሚገነባ ተገልጿል። ከነዚህ በተጨማሪም ስታዲየሙ 4 ዋና መግቢያ በሮች እና 20 መወጣጫ ደረጃዎች እንዳሉት ተነግሯል።

የሜዳ ሳር እና የመሮጫ መም (ትራክ) ግንባታው ገና በሁለተኛ ዙር የግንባታ ሂደት እንደሚካተት በማብራሪያው ሲገለፅ የመጫወቻ ሜዳው ስፋት 105 በ68 ሜትር እንደሆነ ተጠቁሟል። ከሳሩ እና የመሮጫ መሙ በተጨማሪ በቀጣይ ዙር የጣራ ማልበስ፣ የወንበር ተከላ፣ የውሃ እና መብራት መስመር ግንባታ ፣ የመለስተኛ ስታዲየሞች ግንባታ (የእግር ኳስ፣ የቮሊ ቦል፣ ባስኬት ቦል፣ ባድሜንተን እና የቴኒስ ሜዳዎች)፣ የሰው ሰራሽ ሃይቅ ግንባታ፣ የሄሊኮፕተር ማቆሚያ እና ተያያዥ የፊኒሺንግ ስራዎች እንደተካተቱ ተገልጿል።

አንድ ሰዓት ተኩል ከፈጀው የመስክ ጉብኝት በኋላ ስታዲየሙ በሚገነባበት ቦታ ባለ የመሰብሰቢያ አዳራሽ መግለጫ ተሰቷል። መግለጫውንም የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ኤሊያስ ሽኩር፣ አቶ መለስ ለማ እና አቶ አዝመራው ግዛው ሰተዋል።

ግንባታውን የሚቆጣጠሩት ግለሰቦች በቅድሚያ ስታዲየሙ ሙሉ ለሙሉ ተገንብቶ ሲያልቅ የሚኖረውን ገፅታ በአጭር አኒሜሽን በስፍራው ለተገኙ ጋዜጠኞች አስመልክተዋል። ከምስሉ እይታ በኋላ አቶ ኤሊያስ ስለ ስታዲየሙ መጠነኛ ገለፃ ማድረግ ጀምረዋል።

“መንግስት ለስፖርት ዘርፍ የተለየ ትኩረት ሰቶ እየተንቀሳቀሰ ነው። በክልሎችም ሆነ በከተማ አስተዳደሮች ዓለማቀፍ ደረጃን የጠበቁ ስታዲየሞች እየተገነቡ ነው ያሉት። ሀገራችን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ያሉባት እና የተለየ ሃብትን የሚፈልጉ ጉዳዮች ቢኖሩዋትም መንግስት የተለየ ትኩረት ለስፖርቱ ሰቶ የተለያዩ ስታዲየሞች እየተገነቡ ነው። ብሄራዊ ስታዲየማችንም መንግስት ከፍተኛ ሃብት በጅቶ ነው እየተሰራ ያለው። ስታዲየሙ በሁለት ዙሮች ተገንብቶ የሚጠናቀቅ ሲሆን የመጀመሪያ ዙሩ 99 በመቶ ተጠናቋል። መንግስትም ለመጀመሪያ ዙር ግንባታው 2.47 ቢሊዮን ብር ወጪ አድርጎ ስራዎች ተሰርተዋል። የሁለተኛው ዙር ደግሞ ከመጀመሪያው ዙር የበለጠ ሃብት የሚፈልግ ነው። አሁን የሁለተኛውን ዙር ለመጀመር በዝግጅት ላይ ነን። ግምባታውም በተያዘለት ጊዜ የሚጠናቀቅ ከሆነ 900 ቀናት ይፈጁበታል ተብሎ ነው እቅድ የተያዘው። መንግስትም ግምባታውን ለማከናወን 2.4 ቢሊዮን ብር (ለዘንድሮ ዓመት ብቻ) መድቧል።” ብለዋል።

ከኮሚሽነሩ ገለፃ በኋላም በስፍራው የተገኙ የብዙሃን መገናኛ አባላት ጥያቄዎችን ሰንዝረው መግለጫውን ለመስጠት የተሰየሙት ሶስቱ አካላት ምላሾች እና ማብራሪያዎች ተሰተዋል።

ስታዲየሙ ስለተገነባበት ቦታ ረግረጋማነት

ስታዲየሙን ከመገንባታችን በፊት የተለያዩ የአፈር ጥናቶችን አከናውነናል። መሬቱ ይሰምጣል እየተባለ የሚወራው ወሬ ትክክል አደለም። ከ20 በላይ ቦታዎችን ቆፍረን ምርምር አድርገናል። ስለዚህ ይህ ጉዳይ ሊያሳስብ አይገባም።

በግንባታው ስለተሳተፉ ሰራተኞች

በግንባታው 1000 ኢትዮጵያዊያን እና 200 ቻይናዊያን ሰራተኞች ተሳትፈዋል። ከዚህም በኋላ ስታዲየሞችን መስራታችን ስለማይቀር የልምድ ልውውጦችን አድርገናል። ከሰራተኛ አያያዝ ጋር በተያያዘ በተለያዩ ጊዜዎች የሚነሱ ጥያቄዎች ነበሩ። እነሱንም በጊዜው እየተነጋገርን ለመፍታት ሞክረናል።

ስታዲየሙ ካለቀ በኋላ ስለሚጠቀማቸው ቴክኖሎጂዎች

በአሁኑ ሰዓት ዓለም የደረሰበትን ቴክኖሎጂ ለመጠቀም አስበናል። ስታዲየም ከመግቢያ ትኬት ጀምሮ የተለያዩ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን እንጠቀማለን።

ሁለተኛው ዙር ግንባታ መቼ እንደሚጀመር እና መቼ እንደሚጠናቀቅ

በመግለጫው እንደተነገረው ሁለተኛውን ዙር የግንባታ ሂደት ለመጀመር በዝግጅት ላይ ነን። በቅርቡም የኮንትራት ፊርማ ይሆረናል። ስለዚህ ኮንትራቱ ከተፈረመ ከ900 ቀናት በኋላ ስታዲየሙ ይጠናቀቃል።

ስለስታዲየሙ የስያሜ ለውጥ

አደይ አበባ የተባለው ስያሜ ለፕሮጀክቱ የተሰጠው ስያሜ ነው። ነገር ግን ወደፊት ስታዲየሙ ሲመረቅ ስያሜው ይቀጥላል ወይስ የሚለውን አብረን የምናየው ይሆናል።

በዲዛይንም ሆነ በይዞታ ረገድ ውብ ገፅታ ያለው ስታዲየሙ ሙሉ ለሙሉ ከመጠናቀቁ በፊት ለውድድር ክፍት እንደማይሆን ተነግሯል።


© ሶከር ኢትዮጵያ