ቅድመ ዳሰሳ | ወላይታ ድቻ ከ ፋሲል ከነማ

በወላይታ ድቻ እና ፋሲል ከነማ መካከል የሚደረገውን የ7ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

ከመጀመሪያ ሳምንት የሊጉ መርሐ ግብር (ከሲዳማ ቡና ጋር) ውጪ ምንም ጨዋታ ማሸነፍ ያልቻለው ወላይታ ድቻ የጠፋበትን የአሸናፊነት መንገድ ለማግኘት እና ካለበት የወራጅ ቀጠና ለመውጣት ነገ ፋሲልን ይገጥማል።

በፈጣኑ አጥቂ ባዬ ገዛኸኝ የሚመራው ቡድኑ ተጋጣሚን ለማስጨነቅ እንደማይቸገር ይገመታል። ይህ ሮጦ የማይደክመው ተጫዋች ከተሰለፈበት የፊት መስመር በተጨማሪ ወደ ግራ እና ቀኝ በመውጣት የተጋጣሚን የተከላካይ መስመር ትኩረት ለመበታተን የሚያደርገው ጥረት ቡድኑን ሲጠቅም ይስተዋላል። ተጨዋቹ ላይ ፍሬያማ ያለመሆን እና የመባከን እንቅስቃሴዎች ቢስተዋሉበትም ለቡድን አጋሮቹ የሚፈጥራቸው እድሎች የሚደነቁ ናቸው። በነገውም ጨዋታ ለቡድኑ ጠቃሚ እንቅስቃሴዎችን በግሉ እንደሚያደርግ ይጠበቃል። ከባዬ በተጨማሪ በዘንድሮ የውድድር ዓመት ወጣ ገባ ያለ እንቅስቃሴ እያደረገ የሚገኘው ኢድሪስ ሰዒድ ነገ በጥሩ ብቃቱ ላይ ከተገኘ የቡድኑን የማጥቃት እንቅስቃሴ አስፈሪ እንደሚያደርገው ይገመታል።

ባሳለፍነው ሳምንት አዲስ አበባ ላይ በሰበታ ከተማ የተሸነፈው ቡድኑ የግብ አጋጣሚዎችን በአግባቡ የመጠቀም ችግር እንዳለበት ታይቷል። ከዚህ በተጨማሪም በአንፃራዊነት በፍጥነታቸው ዝግ ያሉ ተጨዋቾችን ከወገብ በታች ባለ የሜዳ ክፍል በመያዙ በመከላከሉ ሊቸገር ይችላል። በተለይ ቡድኑ በሚያደርገው የዘገዩ ከማጥቃት ወደ መከላከል የሚደረጉ ሽግግሮች ክፍተቶችን ለተጋጣሚ ሲሰጥ ተስተውሏል። በነገውም ጨዋታ እነዚህ ሁለት ነገሮች ግቦችን በቀላሉ እንዳያስቆጥር እና ግቡን በአግባቡ እንዳይጠብቅ እንዳያደርገው ያሳጋል።

በሊጉ ላይ የሚወዳደሩ ክለቦች ወጥ አለመሆን የጠቀማቸው ፋሲል ከነማዎች ከሜዳቸው ውጪ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎችን ለመገመት አዳጋች ሆኗል። እርግጥ ባሳለፍነው ሳምንት በተደረገ የሊጉ መርሃ ግብር (ከባህር ዳር ጋር) ቡድኑ ሦስት ነጥብ እና ሶስት ጎሎችን በመሸመት ወደ ሰንጠረዥ አናት ቢሸጋገርም አቋሙ ወጣ ገባ ያለ ነው። በነገውም ጨዋታ ቡድኑ የሜዳው ላይ ሃያልነቱን ከሜዳው ውጪ ለመድገም ወደ ሜዳ ይገባል።

የፋሲል ከነማ ዋነኛ የማጥቂያ መሳሪያዎች ሽመክት ጉግሳ እና ሱራፌል ዳኛቸው ቡድኑ የመጀመሪያ የሜዳ ውጪ ድሉን እንዲያገኝ ወሳኝ ናቸው። በተለይ ባሳለፍነው ሳምንት አንድ ጎል የሆነ ኳስ አመቻችቶ ያቀበለው ሽመክት ፍጥነቱን ተጠቅሞ የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ለቡድኑ ጠቃሚ ነው። ሁለቱ ተጨዋቾችም በጨዋታ ተስበው ቦታቸውን ለቀው ለሚወጡት የዲቻ የአማካይ መስመር ተጨዋቾች ፈተናን እንደሚሰጡ ይጠበቃል።

የአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ቡድን ኳስ ሲይዝ አስፈሪነትን ቢላበስም ከኳስ ውጪ የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ለተጋጣሚ ቡድን ምቹ ሁኔታን ሲፈጥር ታይቷል። ይህ ጉዳይ ደግሞ በመከላከሉ ወረዳ ላይ በይበልጥ ስለሚስተዋል በነገው ጨዋታ ሶስት ነጥብ ለጠማው ወላይታ ድቻ ጥቅምን ይዞ ሊመጣ ይችላል።

ፋሲል ከነማዎች እንየው ካሳሁን እና ያሬድ ባዬን በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጪ አድርገዋል።

እርስ በርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለ6 ጊዜያት ሲገናኙ ተመጣጣኝ ሪከርድ አላቸው። በግንኙነታቸው ሁለቱም ክለቦች እኩል 3 ጊዜ ሲሸናነፉ ባለሜዳዎቹ ወላይታ ዲቻዎች 7፣ ፋሲል ከነማዎች ደግሞ 6 ጎሎች ማስቆጠር ችለዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወላይታ ድቻ (4-1-4-1)

መኳንንት አሸናፊ

ፀጋዬ አበራ – አንተነህ ጉግሳ – ደጉ ደበበ – ይግረማቸው ተስፋዬ

ተስፋዬ አለባቸው

ቸርነት ጉግሳ – በረከት ወልዴ – እንድሪስ ሰኢድ – ዳንኤል ዳዊት

ባዬ ገዛኸኝ

ፋሲል ከነማ (4-3-3)

ሚካኤል ሳማኬ

ከድር ኩሊባሊ – ዓለምብርሀን ይግዘው – ሰይድ ሀሰን – አምሳሉ ጥላሁን

በዛብህ መለዮ – ሀብታሙ ተከስተ – ሱራፌል ዳኛቸው

ኦሲ ማውሊ – ሙጂብ ቃሲም – ሽመክት ጉግሳ


© ሶከር ኢትዮጵያ