ቅድመ ዳሰሳ | አዳማ ከተማ ከ ወልዋሎ ዓ/ዩ

አዳማ ከተማ በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም  ወልዋሎን የሚያስተናግድበት ጨዋታን እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

ከብዙዎች ግምት በተቃራኒው ቡድኑ በፋይናንሳዊ ችግሮች እየታመሰም ቢሆን በግሩ ተነሳሽነት  ጨዋታዎች እያደረጉ የሚገኙት አዳማ ከተማዎች በሜዳቸው ላይ ያላቸውን ጥሩ የድል ጉዞ ለማስቀጠል ወደ ሜዳ ይገባሉ።

የአዳማ ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
ተሸነፈ አሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ ተሸነፈ

ባለፉት ጨዋታዎች በሊጉ አጀማመር ላይ ከነበራቸው ኳስን ተቆጣጥሮ የመጫወት አቅም እና ፍላጎት በርካታ መሻሻሎች ያደረጉት አዳማዎች ባለፈው ሳምንት ምንም እንኳ በሲዳማ ቡና ሽንፈት ቢገጥማቸው በጨዋታው የነበራቸው እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጪ ነበር። ሆኖም ቡድኑ ፈጣን አጥቂዎች ካላቸው ቡድኖች ጋር ሲገናኝ በተከላካይ ክፍሉ ላይ ያለውን ድክመት በውጤታቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ ይገኛል። የነገ ተጋጣምያቸው የወልዋሎ አጥቂዎች ምንም እንኳ በቅልጥፍና ረገድ ፈጣኖች ናቸው ባይባልም ቡድኑ በሁለት የአጥቂዎች ጥምረት እንደመጫወቱ ግን ደካማው የአዳማ ተከላካይ መስመርን መፈተኑ አይቀርም።

አዳማዎች በነገው ጨዋታ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስደው በፈጣን አጥቂዎቻቸው አማካኝነት የግብ ዕድል ለመፍጠር አልመው ይገባሉ ተብሎ ሲጠበቅ አብዛኞቹ የቡድኑ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾች በጥሩ ወቅታዊ ብቃት መገኘታቸውም ለቡድኑ ጥሩ ዜና ነው።

አዳማዎች በነገው ጨዋታ ቴዎድሮስ በቀለን በጉዳት ሲያጡ በአንፃሩ ከነዓን ማርክነህ፣ ዳዋ ሆቴሳ እና ጃኮ ፔንዜን ከጉዳት መልስ አግኝተዋል። የምኞት ደበበ መሰለፍ ደግሞ አጠራጣሪ ነው።

የወልዋሎ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
ተሸነፈ ተሸነፈ ተሸነፈ አቻ ተሸነፈ

በውጤት ቀውስ የሚገኙት ቢጫ ለባሾቹ ወደ ወራጅ ቀጠናው ላለመግባት ከዚ ጨዋታ ነጥብ ይዞ መውጣት የግድ ይላቸዋል።

ከጥቂት ቀናት በፊት ከዋና አሰልጣኙ ዮሐንስ ሳህሌ ጋር የተለያዩት ወልዋሎዎች በነገው ጨዋታ በአብርሀ ተዓረ እና ኮማንደር ኪዳነ ሀፍተ  እየተመሩ ወደ ሜዳ ይገባሉ። ሁለቱ ረዳት አሰልጣኞች በዚህ ጨዋታ ይዘውት የሚገቡት አጨዋወት ለመገመት ከባድ ቢሆንም ቡድኑ ካለበት የውጤት ቀውስ እና የመከላከል ችግር አንፃር እምብዛም ለማጥቃት የማይደፍር ቡድን ይዘው ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

አሰልጣኞቹ በጉዳት እየታመሰ የሚገኘው እና የአማራጭ እጥረት ያለበት ቡድንን በቋሚ አሰላለፍ ላይ በአደራደርም ሆነ በተጫዋች ምርጫ ላይ ብዙም ለውጥ ያደርጋሉ ተብሎ አይጠበቅም።

ወልዋሎዎች በነገው ጨዋታ ዓይናለም ኃይለ፣ ፍቃዱ ደነቀ፣ አቼምፖንግ አሞስ፣ ካርሎስ ዳምጠው እና ሰመረ ሀፍታይን በጉዳት አያሰልፉም።

እርስ በርስ ግንኙነት

አራት ጊዜ በሊጉ ተገናኝተው አዳማ ሁለት ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ወልዋሎ አሸንፎ በአንዱ አቻ ተለያይተዋል። አዳማ 5፣ ወልዋሎ 2 አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

አዳማ ከተማ (4-3-3)

ጃኮ ፔንዜ

ሱሌይማን ሰሚድ – ምኞት ደበበ – መናፍ ዐወል – ሱሌይማን መሐመድ

ፉአድ ፈረጃ – አዲስ ህንፃ – ከነዓን ማርክነህ

በረከት ደስታ – ዳዋ ሆቴሳ – ቡልቻ ሹራ

ወልዋሎ (4-2-3-1)

ዓብዱልዓዚዝ ኬይታ

ምስጋናው ወልደዮሐንስ – ዳዊት ወርቁ – ገናናው ረጋሳ – ሄኖክ መርሹ 

ሳሙኤል ዮሐንስ – ራምኬል ሎክ

ብሩክ ሰሙ – ሚካኤል ለማ – ኢታሙና ኬይሙኔ

ጁንያስ ናንጂቡ

© ሶከር ኢትዮጵያ