የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ዙር ክለቦች ዳሰሳ – ድሬዳዋ ከተማ

የ2012 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያውን ዙር በ17 ነጥብ የወራጅ ቀጠና ውስጥ በመሆን ያጠናቀቀው ድሬዳዋን የአጋማሽ ጉዞ ተመልክተናል።

የመጀመሪያ ዙር ጉዞ

ወደ ሊጉ ከተመለሰ ወዲህ ከሰንጠረዡ ወገብ በታች የሚዳክረው ድሬዳዋ ከተማ ዓምናም በመጨረሻዎቹ ሳምንታት ቆይታውን አረጋግጦ በጊዜያዊነት ቡድኑን ተረክበውት የነበሩት አሰልጣኝ ስምዖን ዓባይን በቋሚነት በመቅጠር እና ባለፈው ዓመት በዮሐንስ ሳህሌ ስር ለቡድኑ ፈርመው በዓመቱ መጨረሻ ወደ ወልዋሎ ባመሩት ተጫዋቾች ምትክ ጥቂት ልምድ ያላቸው ተጫዋቾችን ዝውውር በመፈፀም ነበር ዓመቱን የጀመረው። ክለቡ በቅድመ ዝግጅት ውድድር ላይ ደካማ እንቅስቃሴ እንደማድረጉ እና ስብስቡ በአግባቡ ባለመጠናከሩ በፕሪምየር ሊጉ ቆይታውን ለማረጋጠጥ ከባድ የቤት ሥራ እንደሚጠብቀው ፍንጭ የሰጠ ነበር።

የውድድር ዓመቱን ሲጀመር ዋና አሰልጣኙ ከ2011 በዞረ ቅጣት መሰረት ቡድኑን ሁለት ጨዋታ ላይ ሳይመሩ መቅረታቸው ይታወቃል። በተጨማሪም ቡድኑ በተከታታይ የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች ከማድረጉ እና ወሳኝ ተጫዋቾችን በጉዳት ከማጣቱ አንፃር አጀማመሩ ከባድ ሆኖበት ታይቷል።

በመጀመሪያው ሳምንት ወደ ሀዋሳ በማምራት የዓመቱን የመጀመርያ ጎል በኤልያስ ማሞ አማካኝነት አስቆጥረው መምራት ቢችሉም የኋላ ኋላ 2-1 ተሸንፈው ሲወጡ በሁለተኛው ሳምንት በፋሲል ከነማ 5-0 ተሸንፈው በመጥፎ ሁኔታ ጀምረዋል። በሦስተኛው ሳምንት በሜዳቸው ሆሳዕናን በመርታት ያገገሙ ቢመስሉም በአራተኛ ሳምንት በባህር ዳር የደረሰባቸው የ4-1 ሽንፈት መልሰው አጣብቂኝ ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸዋል።

በአምስተኛው ሳምንት በሜዳው በየከቡና ነጥብ ተጋርቶ ከሜዳው ውጪ ሲዳማ ቡናን በማሸነፍ ወደ ጥሩ ጎዳና ተጓዙ ሲባል በድጋሚ በወልዋሎ (በሜዳ) እና ቅዱስ ጊዮርጊስ (ውጪ) በተከታታይ ተሸንፈዋል። ከነዚህ ጨዋታዎች በኋላ በሜዳው አዳማ እኛ ሰበታን ሲያሸንፍ ከሜዳው ውጪ ደግሞ በወልቂጤ እና ወላይታ ድቻ ሽንፈት አስተናግዷል። በተለይ የድቻው ሽንፈት አሰልጣኝ ስምዖን ዓባይ እንዲሰናበቱ ያስገደደ ሲሆን ቀጣዮቹን ሦስት ጨዋታዎች በምክትሉ ፍስሐ ጥዑመልሳን እየተመራ አጠናቋል።

በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ድሬዎች በሜዳቸው ስሑል ሽረ እና ከሜዳቸው ውጪ ከጅማ አባ ጅፋር ጋር ተጋጣሚዎቻቸው በጊዜ ተጫዋቾች በቀይ ካርድ አጥተው በጎዶሎ ቁጥር ቢጫወቱም መጠቀም ሳይችሉ ቀርቸው ከሁለቱ ጨዋታ አንድ ነጥብ ብቻ ሰብስበዋል። በ15ኛው ሳምንት ደግሞ በ90ኛው ደቂቃ የዳኛቸው በቀለ ጎል መቐለን 1-0 አሸንፈው በድል አንደኛውን ዙር አጠናቀዋል።የውጤት ንፅፅር ከ2011 ጋር

ዓምና በዚህ ወቅት በ15 ነጥቦች 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኝ የነበረው ድሬዳዋ ዘንድሮ በደረጃ ከዓምናው ዝቅ ቢልም ነጥብ በማስመዝገብ በ2 ከፍ ያለ ነው። ጎል በማስቆጠር ከዓምናው ጋር ተመሳሳይ ሲሆን የተቆጠረበት ግብ ግን በ9 ከፍ ያለ መሆኑ የኋላ መስመሩ መዳከሙን የሚያሳይ ሆኗል።

የቡድኑ አቀራረብ

በርካታ አማካዮች ያሉት ድሬዳዋ በተለያየ ጊዜ የተለያየ አቀራረብ የሚጠቀም ሲሆን በአመዛኙ ግን 4-4-2 / 4-4-1-1 ምርጫው አድርጎ ሲገባ ይስተዋላል። አብዛኞቹን ተጫዋቾች ከኳስ ጀርባ አድርጎ በመጫወት እንዲሁም የፊት መስመሩን ሚና ሪችሞንድ ኦዶንጎ በሒደት ደግሞ ከሙኅዲን ሙሳ ጋር በማጣመር በረጅሙ በሚጣሉ ኳሶች ላይ ትኩረት የሚያደርግ ቡድን ሲሆን የመስመር ተጫዋቾችን በሚጠቀምባቸው ወቅቶች ደግሞ በ4-2-3-1 አሰላለፍ ሲጠቀምም ተስተውሏል።

ቡድኑ የተጠቀመበት 4-4-1-1 የመጀመርያ ሳምንታት ላይ ስኬታማ አለመሆኑን ተከትሎ በ4-4-2 ሪችሞንድ እና ሙህዲንን ከፊት አጣምረው ወደ መሐል ሜዳ ጠበብ ያለ የአማካይ ጥምረት በመፍጠር የውድድር ዘመኑን አጋምሰዋል። በተለይም በዚህ የጨዋታ እንቅስቃሴ ወቅት ቡድኑ የሪችሞንድን ጉልበት እንዲሁም የሙህዲን ፍጥነት ለመጠቀም ጥረት ያደረጉ ሲሆን ከመስመር ወደ መሐል ሜዳ እየተጠጉ የሚጫወቱት አማካዮችም በሚፈለገው ደረጃ ባይሆንም የማጥቃቱን እነሰቅስቃሴ ለማገዝ ጥረት አድርገዋል። በዛው ልክ መስመር በኩል የኋላ ክፍሉ ያለው ተጋላጭነትም የታየበት አጋማሽ ነበር።

በተጫዋቾች ምርጫ ረገድ በግብ ጠባቂ ስፍራ ላይ አምበሉ ሳምሶን አሰፋ በገጠመው ጉዳት ባልተሰለፈባቸው ጨዋታዎች በፍሬው ጌታሁን ከመተካቱ በቀር ቀዳሚ ተመራጭ ነበር። በተከላካይ ሥፍራ የያሲን ጀማል – ፍሬዘር ካሳ – በረከት ሳሙኤል – አማረ በቀለ ጥመረት ቀዳሚ ተመራጭ መሆኑ የተስተዋለ ሲሆን በረከት በጉዳት ባልነበረባቸወ ጨዋታዎች ያሬድ ዘውድነህ እና ዘሪሁን አንሼቦ ተጫውተዋል።

በአማካይ ሥፍራ ላይ ቢንያም ፆመልሳን/ያሬድ ታደሰ – ዋለልኝ ገብሬ – ፍሬድ ሙሸንዲ – ኤልያስ ማሞ ጥምረት የሚጠቀስ ሲሆን አማኑኤል ተሾመንም በጥቂት ጨዋታዎች ተጠቅመዋል። ቡድኑ በአንዳንድ ጨዋታዎች ላይ የአማካይ ክፍሉን ቅርፅ በሚለውጥባቸው ጊዜያት ያሬድ ታደሰ እና ሳሙኤል ዘሪሁን ከመስመር እየተነሱ ሲያጠቁ ተስተውሏል። በአጥቂ ስፍራ ደግሞ ጋናዊው ሪችሞንድ አዶንጎ እና ወጣቱ ሙኅዲን ሙሳ ቀዳሚ ተመራጭ ነበሩ።

ጠንካራ ጎን

የተጫዋቾች የተናጠል ጥረት ካልሆነ እንደ ቡድን የድሬዳዋ ከተማን ጠንካራ ጎን ለማውጣት አዳጋች ነው። ጎሎች የሚቆጠሩት ከቆሙ ኳሶች እና በረጅሙ የሚጣሉትን ኳሶች አጥቂዎቹ በግል ጥረታቸው ከተከላካዮች ጋር በመታገል የሚያስቆጥሯቸው ናቸው። በተከላካይ መስመሩም ተጫዋቾቹ በተናጠል በሚያሳዩት ተጋድሎ በአንዳንድ ጨዋታዎች ጎል ሳይቆጠርበት መውጣት ቻለ እንጂ እንደ ቡድን ጥሩ የመከላከል አደረጃጀት ሲፈጥር አልተስተዋለም።

ደካማ ጎኖች

ምንም እንኳ በመጨረሻዎቹ ተከታታይ ጨዋታዎች መሻሻል ቢያሳይም የተከላካይ መስመሩ ደካማ እንደነበር የተቆጠሩበት ጎሎች ምስክር ናቸው። በጨዋታ በአማካይ 1.7 ጎሎች የሚቆጠርባቸው ድሬዳዋዎች በሊጉ የነሱን ያህል በርካታ ጎል ያስተናገደ የለም። የስብስብ ደረጃ ጥሩ የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቾች የያዘው ቡድኑ በአጨዋወት ደረጃ ከአማካይ ክፍሉ በቂ የሆነ ሽፋን የማያገኝ መሆኑ በቀላሉ ተጋላጭ እንዲሆን አድርጎታል።

የጎል ዕድሎችን የሚፈጥርበት የጠራ የማጥቃት እቅድ የሌለው ቡድን መሆኑ በአጋማሹ በስፋት ታይቷል። በቅብብል ወደ ሳጥን ለመድረስ የሚቸገር ቡድን ሲሆን ጎሎችን ለማግኘት የቆሙ ኳሶችን ዋንኛ መሳርያ ሲያደርግ ይስተዋላል። በተጨማሪ ከርቀት ለአጥቂዎቹ የሚጣሉ ኳሶችን እንደ እቅድ ይዞ የሚገባ መሆኑ በተጋጣሚ ተከላካዮች ቁጥጥር ስር በቀላሉ እንዲገቡ አድርጓቸዋል።

በሁለተኛ ዙር ምን ይጠበቃል?

ለሁለተኛ ዙር ቡድኑን ከወዲሁ የማጠናከር ሥራ የጀመረው ድሬዳዋ ክፍተቱን ሊደፍኑ የሚችሉ ጥሩ ዝውውሮችን እየፈፀመ ይገኛል። ሆኖም የዋና አሰልጣኝ ቅጥር ጉዳይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው። ጊዜያዊው አሰልጣኝ ፍስሐ ጥኡመልሳንን ማስቀጠል አልያም በቋሚነት አዲስ አሰልጣኝ ማምጣት የመጀመርያ የቤት ስራው መሆን ይገባው ነበር።

ቡድኑን ለማጠናከር እስካሁን በተከላካይ እና አጥቂ ስፍራዎች ላይ ተጫዋቾች ያስፈረመው ቡድኑ የቡድን ሚዛን በሚጠብቅ እና በኤልያስ ማሞ ላይ ብቻ የተንጠለጠለው የማጥቃት እኖቅስቃሴን የመምራት ኃላፊነት የሚጋራ ተጫዋች ላይ ትኩረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

በሁለተኛው ዙር እንደ ረመዳን ናስር ያሉ ወሳኝ ተጫዋቾቻቸውን የሚያገኙት ድሬዎች በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎችን በሜዳቸው የሚያደርጉ መሆናቸው የምስራች ነው ማለት ይቻላል። ከነዚህ ጨዋታዎች ከፍተኛውን ነጥብ መሰብሰብ ከቻሉም በቀጣይ ለ21 ቀናት ሊጉ የሚቋረጥ መሆኑ ክፍተቶቻቸውን ለመድፈን ጊዜ እንዲያገኙ እንደሚረዳቸው ይጠበቃል።

የ1ኛ ዙር ኮከብ ተጫዋች

ኤልያስ ማሞ፡ በቅርቡ ውሉን በድጋሚ ያራዘመው ኤልያስ ማሞ በግሉ ጥሩ ጊዜ ማሳለፍ ችሏል። የአጥቂ አማካይ በመሆን ያገለገለው ኤልያስ ለቡድኑ ሁሉንም ጨዋታ ያደረገ ሲሆን እንደ ቡድን እገዛ ባያገኝም የማጥቃት እንቅስቃሴ ለመምራት የሚያደርገው ጥረት ጥሩ የሚባል ነበር። በሁለተኛው ዙር ቡድኑን በሱ ብቃት ዙርያ መገንባት ከተቻለ የቡድኑ ደካማ ጎን የሆነው የማጥቃት እንቅስቃሴን እንደሚያሻሽል ይታመናል።

ተስፋ የሚጣልበት ተጫዋች

ሙኅዲን ሙሳ፡ ለሊጉ አዲስ ባይሆንም የመጫወት እድል በቅጡ ያገኘው ዘንድሮ ነው። ወጣቱ አጥቂ ያገኘውን እድል በአግባቡ በመጠቀም የቡድኑ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ መሆን የቻለ ሲሆን በሁለተኛው ዙር ይበልጥ በተጫዋቹ ላይ እምነት ማሳደር ለቡድኑ የሚሰጠው አበርክቶት እንዲጨምር ማድረጉ አይቀሬ ነው።

© ሶከር ኢትዮጵያ